«የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እንዴት ይሁን? የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ባለቤትነትስ ለማን ይሰጥ? የክልሎች አወቃቀር እንዴት ይሁን እና የጸጥታ ተቋማት እንዴት ገለልተኛ ይሁኑ?» ለሚሉት ጥያቄዎች በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ምክክር ላይ የተሳተፉ ጉባኤተኞች የተለያዩ ምክረ ሃሳቦችን አስቀምጠዋል።
- 1 day ago
- 2 min read
ሐምሌ 21 2018
«የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እንዴት ይሁን? የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ባለቤትነትስ ለማን ይሰጥ? የክልሎች አወቃቀር እንዴት ይሁን እና የጸጥታ ተቋማት እንዴት ገለልተኛ ይሁኑ?» ለሚሉት ጥያቄዎች በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ምክክር ላይ የተሳተፉ ጉባኤተኞች የተለያዩ ምክረ ሃሳቦችን አስቀምጠዋል።
የተቀመጡት ምክረ ሃሳቦች በጉባኤተኞች የጸደቁ ሳይሆኑ፣ በሂደት ላይ ባለው ምክክር በንዑሳን እና ጥቃቅን ቡድኖች ደረጃ ከተሳታፊዎች የቀረቡ አማራጭ ምክረ ሃሳቦች ናቸው።
የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በተመለከተ የተለያዩ አማራጮች ቀርበዋል።
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ውስጥ የሂጅራ ወይም የእስላማዊ የዘመን አቆጣጠር ይካተት፣ «ዓመተ ምህረት» የሚለው ይቅርና አሁን ያለው አቆጣጠር ይቀጥል፣ እንዲሁም ከእስልምናም ሆነ ከክርስትና ሃይማኖቶች ነፃ የሆነ የዘመን አቆጣጠር እንከተል የሚሉ ምክረ ሃሳቦች መቀረባቸውን ተሳታፊዎች ነግረውናል።
የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋን ባለቤትነት ጉዳይ በተመለከተም የተለያዩ አማራጮች ቀርበዋል።
ከሲዳማ ክልል የመንግስት አካላት ተወካይ የሆኑት አቶ ደምሴ ደንግሶ፤ አዲስ አበባን በተመለከተ አንዳንዶች «ወደ ኦሮሚያ ትካለል»፣ ሌሎች ደግሞ «ራሷን ችላ ክልል ትሁን» የሚሉ ምክረ ሃሳቦችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ስለሆነች እና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስት ይሁን የሚል ምክረ ሃሳብ መቅረቡን ያነሱት ተሳታፊው፣ ከተማዋ «መሃል ኦሮሚያ ላይ ስለሆነች ወደ ኦሮሚያ ትካለል» የሚሉ ሃሳቦችም መቅረባቸውን አስረድተዋል።
የድሬዳዋ ከተማን ጉዳይ በተመለከተ ደግሞ ተጠሪነቷ በቀጥታ ለፌደራል መንግስት እንዲሆን እና የስልጣን ክፍፍሉም ፍትሃዊ እንዲሆን የሚል ምክረ ሃሳብ መቅረቡን የመንግስት ተወካዩ አቶ ደምሴ ጠቅሰዋል ።
የክልሎች አወቃቀር እንዲሁም የመንግስት አስተዳደር ስርዓትን በተመለከተም የተለያዩ አማራጮች ቀርበዋል።
የጎጎት ለጉራጌ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብራር፣ «ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት መከተል አለባት» የሚለው ሃሳብ እሳቸው በነበሩበት ቡድን የውይይት ወቅት የሚበዛው ተሳታፊ የተስማማበት ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
ግን «የትኛው የፌደራሊዝም ስርዓት ይሁን?» በሚለው ላይ ብዙ አማራጮች የቀረቡበት እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህም አንዳንዶች «አሁን ያለው ስርዓት ይቀጥል»፣ ቀሪዎቹ «አሁን ያለው ተገምግሞ ጥገና ይደረግበት»፣ ሌሎች ደግሞ «አሁን ያለው የፌደራል ስርዓት ሚዛናዊ አይደለም፤ የእርስ በእርስ ክፍፍሉንም አስፍቷል፤ ስለዚህ ክልሎች የሚደራጁበት መንገድ እንደገና ይከለስ» የሚሉ ምክረ ሃሳቦችን መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወክለው መሳተፋቸውን የተናገሩት አቶ ነፃነት ጠባሰው የተባሉ ተሳታፊ፣ እሳቸው ያሉበት ቡድን በመንግስት አደረጃጀት እና ቅርፅ አጀንዳ ላይ እየተወያየ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።
አሃዳዊ ስርዓት እንከተል፣ ክልላዊ ፓርቲዎች አይኑሩ፣ አሁን ያለው የክልል አወቃቀር ይቀጥል፣ ክልሎች በቋንቋ ሳይሆን ከአቀማመጣቸው ይመስረቱ፣ እና ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሳይሆን «ሰሜን፣ ምዕራብ፣ ደቡብ፣ ምስራቅ እና መሃል» በመባል ለአምስት ትከፈል የሚሉ አማራጮች መቅረባቸውን ተሳታፊው ነግረውናል።
የጸጥታ ተቋማት ገለልተኛ እንዲሆኑም ምክረ ሃሳብ ተሰጥቷል።
በሰላም ግንባታ አጀንዳ ስር ከተወያዮች ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ አሳምነው ተሾመ «ከአጼዎቹ ጀምሮ የጸጥታ ተቋማት ለአንድ ወገን ያደሉ» መሆናቸውን አስረድተዋል።
ይህ ችግር በደርግ እና በኢሕአዴግ ዘመነ መንግስትም ስለቀጠለ፣ ይህ እንዲቀር የጸጥታ ተቋማት የአንድ መንግስት አገልጋይ ሳይሆኑ የአገር ሆነው እንዲቀጥሉ ምክረ ሃሳብ ተሰጥቷል ብለዋል።
ያን ማድረግ ሲቻል ስርዓት በተቀየረ ቁጥር የሚበተን እና እንደ አዲስ የሚቋቋም የጸጥታ ተቋም እንዳይኖር ያደርጋል ብለዋል።
ሚቆሙ ሃውልቶች እና የአዲስ አበባ ከተማ የቦታዎች ስያሜን በተመለከተም ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
መጠሪያቸው ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች ሁሉን ይመስሉ፣ እንዲሁም የሚቆሙ ሃውልቶች ጠብ አጫሪ እና አንድን ወገን ብቻ የሚወክሉ መሆን የለባቸውም የሚሉ ምክረ ሃሳቦች መቅረባቸውን የነገሩን ደግሞ አቶ ፈይሰል አብዱላዚዝ ናቸው።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚቆሙ ሃውልቶች የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣላቸው እና «የአገር ጀግና» የሚል መጠሪያ ለሚሰጣቸው ኢትዮጵያውያን መስፈርት ይዘርጋ የሚሉ ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አንዳንድ አካላት የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን የመጨረሻ ውሳኔ አድርገው የሚያቀርቡ እንዳሉ እና ይህም ስህተት መሆኑን አስገንዝበዋል ።
በአጀንዳዎች ላይ ውሳኔ ተደርሷል ተብሎ የሚሰራጨው መረጃ ሃሰት መሆኑን ያብራሩት ኮሚሽነሩ፣ ለውሳኔ ሂደቱ ገና መሆኑን አክለዋል።
ያሬድ እዳሻው
_edited.jpg)


Comments