top of page

ሐምሌ 18 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Jul 25
  • 2 min read

ፈረንሳይ ለፍልስጤም ነፃ አገርነት ይፋዊ እውቅና ልትሰጥ ነው፡፡


ፈረንሳይ ለፍልስጤም ነፃ አገርነት እውቅና ለመስጠት መሰናዳቷን ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤክስ ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባኖሩት መልዕክት እወቁልኝ ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በማክሮን መልዕክት መሰረት ፈረንሳይ በመጪው መስከረም ወር ለፍልስጤም ነፃ አገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ተጠቅሷል፡፡

ree

ለፍልስጤም ነፃ አገርነት ይፋዊ እውቅና በመስጠትም ፈረንሳይ ከቡድን 7 አባል አገሮች የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች፡፡


ፈረንሳይ መስከረምን የመረጠችው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄድበት ጊዜ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡


የፍልስጤም መሪዎች የማክሮንን ውሳኔ በእጅጉ አድንቀዋል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን ሽብርን መሸለም ነው ሲሉ የማክሮን ውሳኔ ማጣጣላቸው ተሰምቷል፡፡



የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በፓርላማው ሰሞኑን ከፀደቀ በኋላ ስራ ላይ እንዲውል የፈረሙበት ህግ እንዲሻርላቸው መልሰው ለፓርላማው ላኩት ተባለ፡፡


ፕሬዘዳንቱ የመሻሪያ ረቂቅ ያቀረቡበት አወዛጋቢው ህግ የአገሪቱን የምዝበራ እና የብልሹ አሰራር ተካላካይ መስሪያ ቤቶችን በአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስር የሚያደርግ እንደነበር አልጀዚራ አስታውሷል፡፡


ፕሬዘዳንቱ ህጉ ላይ ፊርማቸውን ካኖሩበት ደቂቃ ጀምሮ ህዝቡ በርዕሰ ከተማዋ ኪየቭ እና በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ግልብጥ ብሎ በመውጣት ተቃውሞ እንዳቀረበባት ተሰምቷል፡፡


ተቃውሞው ህጉ የምዝበራ መከላከሉን ተግባር በእጅጉ ያዳክማል በሚል መንፈስ የተካሄደ ነው ተብሏል፡፡


የዩክሬይን አጋሮች የሚባሉት አገሮች እና አካላት ጭምር በምዝበራ ተከላካዮቹ መስሪያ ቤቶች ነፃነት መገደብ ደስተኞች እንዳልነበሩ ተጠቅሷል፡፡


ዜሌንስኪ በተፈጠረባቸው ህዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ ለአገሪቱ ፓርላማ የመሻሪያ ረቂቅ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡



በቆጵሮስ የሰደድ እሳት እየተዛመተ ነው፡፡


የሰደድ እሳቱ ሁለት ሰዎችን መግደሉን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡


በቃጠሎው አካላዊ ጉዳት የገጠማቸው ሌሎች 16 ሰዎች በሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡


በአገሪቱ የሙቀቱ መጠን ወደ 44 ዲግሪ ሴሌሺየስ እንደሚያሻቅብ መተንበዩ የሰደድ እሳቱን ሊያባብሰው እንደሚችል ተገምቷል፡፡


የአገሪቱ መንግስት የአቅራቢያው አገሮች የሰደድ እሳቱን ለመከላከል እንዲያግዙት የእርዳታ ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡


እስራኤል የእሳት አደጋ ተከላካዮቻችንን ወደ ቆጵሮስ እንልካለን ካሉት መካከል እንደሆነች ተጠቅሷል፡፡



የካምቦዲያ ጦር በወሰን አካባቢ በታይላንድ ተይዞብኝ የቆየውን ግዛት መልሼ በእጄ አስገብቻለሁ አለ፡፡


በአሁኑ ጊዜ ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት እያመሩ መሆኑን አናዶሉ ፅፏል፡፡


የታይላንድ መንግስት ካምቦዲያ ባልታወጀ ጦርነት በከፈተችብን ጥቃት 10 ሰላማዊ ሰዎች እና ሁለት ወታደሮች ተገድለውብኛል ማለቱ ተሰምቷል፡፡


ቀደም ሲልም የሁለቱ አገሮች ጦሮች በወሰን አካባቢ ቁርቋሶ ጀምረው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


ሁለቱም አገሮች ጠብ አጫሪነት ተፈፅሞብናል በሚል እርስ በርስ እየተካሰሱ ነው፡፡


ቻይና ፣ ማሌዥያ እና ጃፓን ሁለቱ አገሮች ከሀይል አማራጭ ተቆጥበው ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ እንዲደራደሩ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡



በጦርነቱ ምክንያት ከሱዳኗ ርዕሰ ከተማ ካርቱም የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበላቸው፡፡


የካርቱም ነዋሪዎች ወደ መዲናዋ እንዲመለሱ ጥሪ ያቀረቡት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባቢከር ሳምራ እንደሆኑ አሽራቅ አል አውሳት ፅፏል፡፡


ከተማይቱ ከ2 አመታት ላላነሰ ጊዜ የውጊያ አውድማ ሆኖ ቆይታለች፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር በካርቱም ሙሉ ቁጥጥሩን ያሰፈነው ከጥቂት ወራት በፊት ነው፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር ከ2 አመታት በላይ ከRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጋር ውጊያ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡


በካርቱም ሲካሄድ በነበረው ጦርነት የተነሳ በአሁኑ ወቅት የሱዳን መንግስት አስተዳደራዊ ማዕከሉን ወደ ምስራቃዊቱ የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳን ማዞሩ ይነገራል፡፡


የካርቱም ተፈናቃዮች ግን ወደ ከተማቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል ተብሏል፡፡


የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ በካርቱም የተሟላ የፖሊስ ሀይል እንደተመደበም ተናግረዋል፡፡



በናይጀርያ ኒጀር ግዛት የተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ 13 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡


ወረርሽኙ በግዛቲቱ 6 አካባቢዎች እየተዛመተ መሆኑን የጤና ሹሞች መናገራቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


በግዛቲቱ የኮሌራ ወረርሽኙ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው ተብሏል፡፡


የኒጀር ግዛቱ የኮሌራ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወደ አንደኛ ወሩ መቃረቡ ተጠቅሷል፡፡


የንፁህ ውሃ እጦት ፣ የንፅህና መጓደል እና የህክምና ተግባሩ መዳከም ለወረርሽኙ መዛመት በምክንያት ቀርበዋል፡፡


በኒጀር ግዛት አስተዳደሩ ወረርሽኙ ባየለባቸው አካባቢዎች የለይቶ ማከሚያ ጣቢያዎችን እየቋቋመ ነው ተብሏል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page