top of page

ሐምሌ 15 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Jul 22
  • 2 min read

ዩክሬይን እና ሩሲያ ወደ ሰላም ንግገራቸው ሊመለሱ ነው፡፡


ሁለቱ አገሮች ወደ ሰላም ንግግራቸው እንደሚመለሱ የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ መናገራቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የሰላም ንግግሩ የጦር ምርኮኞች ልውውጥንም ይጨምራል ተብሏል፡፡

ree

ሩሲያ እና ዩክሬይን ከጥቂት ወራት በፊት በቱርክ ኢስታምቡል የሰላም ንግግር ጀምረው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


የአሁኑም ንግግር በዛው በቱርክ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ሩሲያ የዩክሬይኑን ጦርነት እንድታቆም የ50 ቀናት የጊዜ ገደብ ማስቀመጣቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡


ዜሌንስኪ ከሩሲያ ጋር የሰላም ድርድራችንን እንቀጥላለን ቢሉም ከክሬምሊን በኩል በዚህ ረገድ የተሰማ አስተያየት የለም ተብሏል፡፡



በሶማሊያ የፑንትላንድ አስተዳደር ለሞቃዲሾው የሶማሊያ መንግስት ሊሰጥ በመርከብ ሲጓጓዝ የነበረን ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ያዝኩኝ አለ፡፡


የኮሞሮስን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልበው እና በፑንትላንድ አስተዳደር የተያዘው መርከብ ከቱርክ ለሶማሊያ መንግስት የተላከ የጦር መሳሪያ የጫነ እንደሆነ ዘ ማሪታይም ኤክሴኩቲቭ ድረ ገፅ ፅፏል፡፡


ጭነቱ ብረት ለበስ የጦር ተሽከርካሪዎችንም ይጨምራል ተብሏል፡፡


በፑንትላንድ አስተዳደር የተያዘው የጭነት መርከብ በአሁኑ ወቅት በቦሳሶ ወደብ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡


እንደሚባለው በህገ መንግስታዊ ጉዳዮች በተፈጠረ አለመግባባት የፑንትላንድ አስተዳደር ለሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት እውቅና ከነፈገው ከአመት በላይ ሆኖታል፡፡



የየመን ሁቲዎች ትናንት በ5 የእስራኤል ዒላማዎች ላይ በሰው አልባ በራሪ አካላት /ድሮኖች/ ጥቃት ፈፅመናል አሉ፡፡


ሁቲዎቹ የድሮን ጥቃት ፈፅመናል ያሉት እስራኤል የሁቲዎቹ ይዞታ የሆነውን የሁዴይዳን ወደብ መደብደቧን ተከትሎ ነው መባሉን አናዶሉ ፅፏል፡፡


የየመን ሁቲዎች በእስራኤል ላይ የድሮን ጥቃት ፈፅመናል ካሉባቸው ስፍራዎች መካከል የቴል አቪቩ ቤን ጉሪዮን ኤርፖርት አንዱ ነበር ተብሏል፡፡


በእስራኤል የሁዴይዳ ድብደባም ሆነ በሁቲዎቹ የድሮን አፀፋ ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡


እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ከከፈተች አንስቶ ሁቲዎቹ ለፍልስጤማውያን ድጋፋቸውን ለማሳየት ከእስራኤል ጋር በከባዱ ሲጋጩ ቆይተዋል፡፡


ግጭቱ ከተቀሰቀሰ አንስቶ እስራኤል በሁቲዎቹ ይዞታ ላይ ከባድ ድብደባዎችን ስትፈፅም የትናንቱ 12ኛዋ ነው ተብሏል፡፡


ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡



በባንግላዴሽ ለልምምድ የተነሳ የአየር ሀይሉ አውሮፕላን በመዲናዋ ዳካ በመከስከሱ በጥቂቱ የ27 ሰዎች ሕይወት አለፈ ተባለ፡፡


አደጋው የደረሰው ለልምምድ ተነሳ የተባለው F7 ጄት በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በመከስከሱ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉ ከተረጋገጠው ሌላ ከ170 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የተለያዩ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ታውቋል፡፡


አካላዊ ጉዳት ከገጠማቸው መካከል 50ዎቹ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ተብሏል፡፡


ሆስፒታል ከገቡት መካከል ለሕይወታቸው አስጊ የሆነ ጉዳት የገጠማቸው እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡


አብዛኞቹም የአደጋው ሰለባዎች ሕፃናት እና ወጣት ተማሪዎች ናቸው ተብሏል፡፡


አየር ሀይሉ አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ባጋጠመው ሜካኒካዊ እክል ነው የሚል የቅድሚያ መግለጫ ማውጣቱ ተሰምቷል፡፡


የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት ግን ጉዳዩ በብርቱ እንዲመረመር እናደርጋለን ብለዋል፡፡


ባንግላዴሽ በአደጋው ምክንያት ዛሬን በብሔራዊ ሐዘን ታሳልፋለች፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page