ሐምሌ 10 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Jul 17
- 2 min read
የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የቆዩትን ዴኒስ ሺማይሐልን የመከላከያ ሚኒስትር አደረጓቸው፡፡
ዜሌንስኪ ቀደም ብለው የኢኮኖሚ ሚኒስትር የነበሩትን ዩሊያ ሲቪሪዴንኮን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ማጨታቸውን አናዶሉ አስታውሷል፡፡

የሚኒስትሮቹ ሹም ሽር እና የአመራር ለውጥ ለፓርላማው ይሁንታ መቅረቡ ታውቋል፡፡
የቀድሞው የመከላያ ሚኒስትር ኡስቴም ኡሜሮቭ በአሜሪካ የዩክሬይን አምባሳደር እንደሚሆኑ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የአመራር ለውጡ በእጅጉ አስፈላጊያችን ነው ብለዋል፡፡
ዩክሬይን ከ3 አመታት በላይ ከሩሲያ ጋር በጦርነት ላይ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡
እስራኤል በሶሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር ላይ ያነጣጠረ ድብደባ ፈፀመች፡፡
የሶሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር በርዕሰ ከተማዋ ደማስቆ በቤተ መንግስቱ አቅራቢያ እንደሚገኝ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በእስራኤል ድብደባ በጥቂቱ 3 ሰዎች ሲገደሉ ከ30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
እስራኤል ቀደም ሲል የሶሪያ መንግስት ወታደሮች በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የድሩዝ ማህበረሰብ አባሎች መኖሪያ ከሆነችው ሱዌይዳ እንዲወጡ አስጠንቅቃ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ሰሞኑንም በሱዌይዳ አቅራቢያ በሶሪያ መንግስት ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈፀሟ ተነግሯል፡፡
እስራኤል የድሩዝ ማህበረሰብ አባሎችን ከጥቃት እጠብቃለሁ ባይ ነች፡፡
አገሪቱ በሶሪያ ላይ የፈፀመችውን ድብደባ ቱርክ ፣ ሊባኖስ እና ኢራቅ እንዳወገዙት ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካ የመከላከያ ሹሞች የደማስቆው ድብደባ በእኛም ይሁንታ የተፈፀመ ነው ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
በጋዛ ሰርጥ በአንድ የሰብአዊ እርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል በተፈጠረ ተገፋፍቶ መረጋገጥ በጥቂቱ የ20 ሰዎች ሕይወት አለፈ ተባለ፡፡
የሰብአዊ እርዳታ ማከፋፈሉ ተግባር የሚከናወነው በምህፃሩ GHF በተሰኘው ድርጅት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ድርጅቱ በአሜሪካ እና በእስራኤል እንደሚደገፍ ይነገራል፡፡
የGHF የሰብአዊ እርዳታ ስርጭት በውጥንቅጥ የተሞላ ሆኖ መቆየቱ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
ድርጅቱ በካን ዩኒስ አቅራቢያ የእርዳታ ማከፋፈያው በተፈጠረው ተገፋፍቶ መረጋገጥ ለሰዎች ሞት ምክንያቱ የሐማስ ደጋፊዎች የፈጠሩት ውዥንብር ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የሐማስ ሰዎች ደግሞ GHF እኛን የሚከሰው የራሱን ወንጀል ለመሸፋፈን አቅዶ ነው ማለታቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
የሶሪያው ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት አህመድ አልሻራ ሰላምን እናስቀድም ብለን እንጂ በጭራሽ ጦርነትን አንፈራም አሉ፡፡
የአልሻራ አስተያየት የተሰማው እስራኤል በደማስቆ በሚገኘው የሶሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ አንደሆነ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
በእስራኤል የደማስቆ ድብደባ በጥቂቱ አራት ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡
እስራኤል በሶሪያ መንግስት ጦር ላይ ጥቃት ያደረሰችው በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሚኖሩት የድሩዝ ማህበረሰብ አባሎች ላይ የሚፈፅመውን ጥቃት ለማስቆም እንደሆነ ሹሞቿ ተናግረዋል፡፡
አልሻራ እስራኤል ደርሶ በእኛ የውስጥ ጉዳይ ምን ጥልቅ አደረጋት እያሉ ነው፡፡
በድሩዞቹ መኖሪያ ሰሞኑን በተፈጠረ ግጭት 170 ያህል ሰዎች እንደተገደሉ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኢስዋቲኒ መንግስት አዎ ከአሜሪካ የተባረሩ 5 ሰነድ አልባ ስደተኞችን ተቀብያለሁ አለ፡፡
ሰነድ አልባዎቹ በአሜሪካም ብርቱ ብርቱ ወንጀሎችን በመፈፀም በእስር ቤት የቆዩ እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡
ኢስዋኒ እንደደረሱም እስር ቤት እንደገቡ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
የሰነድ አልባዎቹ ስደተኞች ተቀባይ የሆነችው አፍሪካዊት አገር ሹሞ እስረኞቹን የተቀበልነው ከአሜሪካ መንግስት ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ሰነድ አልባዎቹ የእስር ጊዜያቸው እንዳበቃ በአለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት /IOM/ እና በአሜሪካ መንግስት ትብብር ወደ መነሻ አገራቸው እንዲመልሷቸው ተናግረዋል፡፡
አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) በዚህ በኩል የሰጠው አስተያየት እንደሌለ ተጠቅሷል፡፡
በኢራቅ ኩት ከተማ በአንድ የገበያ ማዕከል የደረሰ ከባድ ቃጠሎ 60 ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡
በርካቶች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ከባድ ቃጠሎ ያጋጠመው የገበያ ማዕከል ከተከፈተ ገና 5 ቀኑ ነው ተብሏል፡፡
አብዛኞቹ የአደጋው ሰለባዎች ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸው ታውቋል፡፡
አምስት የአንድ ቤተሰብ አባሎች ከሟቾቹ መካከል ናቸው ተብሏል፡፡
ቃጠሎው በምን ምክንያት እንደተቀሰቀሰ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም፡፡
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ የ3 ቀናት ግዛታዊ ሐዘን ማወጃቸው ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments