ህዳር 1 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 1 day ago
- 2 min read
በአውሮፓ አገሮች ታግዶ የሚገኘው የሩሲያ ገንዘብ ለዩክሬይን በብድር የመሰጠቱ ሀሳብ ከስሎቫኪያ በኩል ጠንካራ ተቃውሞ ገጠመው፡፡
በአውሮፓ ህብረት ዘንድ ታግዶ ከሚገኘው የሩሲያ ገንዘብ 140 ቢሊዮን ዩሮው ለዩክሬይን የጦር መደገፊያ በብድር እንዲሰጣት ምክር ከተያዘ መቆየቱን አናዶሉ አስታውሷል፡፡
የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ ግን እኛ የዚህ ውጥን አካል አይደለንም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

ከዚህ ይልቅ ለዩክሬይኑ ጦርነት ማብቃት ጥረቱ ቢበረታ ይሻላል ብለዋል ፊኮ፡፡
የታገደው የሩሲያ ገንዘብ ለዩክሬይን የጦር መደገፊያነት በብድር በሚሰጥበት መላ በአውሮፓ ህብረት መድረክ በመጪው ወር በታላቁ እንደሚመከርበት ታውቋል፡፡
ገንዘቡ ለዩክሬይን በብድር እንዲፈቀድላት የሁሉንም የህብረቱ አባል አገሮች ሙሉ ስምምነት እንደሚሻ ተጠቅሷል፡፡
የሱዳኑ RSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል በሰሜናዊ ዳርፉር ኤል ፋሸር ከተማ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ እልቂት እንዲፈፀም አዟል ባለው የጦር ሹሙ ላይ ምርመራ እያደረኩበት ነው አለ፡፡
ፈጥኖ ደራሹ ምርመራ እያደረገበት የሚገኘው የጦር አዛዡ አቡ ሉሉ የተባለው እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
የግለሰቡ እውነተኛ ሙሉ ስም አልፋታህ አብዱላ ኢድሪስ እንደሚሰኝ ተጠቅሷል፡፡
ግለሰቡ በኤልፋሸር ከተማ ከ2 ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎችን መጨረሱን አምኗል ተብሏል፡፡
RSF በግለሰቡ ላይ ተጨማሪ ምርመራዎችን አድርጌ ግኝቴን አሳውቃለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ኤል ፋሸርን የተቆጣጠራት በቅርቡ ነው፡፡
በከተማይቱ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመው እልቂት በRSF ላይ ውግዘት እና ተቃውሞ እንዳበዛበት ይነገራል፡፡
በአሜሪካ የመንግስት አገልግሎት መስተጓጎሉ ሊያበቃ ነው፡፡
አገሪቱ በመንግስት አገልግሎት መስተጓጎል ውስጥ የቆየችው በጀት እና የወጪ ዝርዝሩ ባለመፅደቁ የተነሳ ነው፡፡
በአሜሪካ ኮንግረስ ሪፖብሊካውያን እና ዴሞክራቶቹ በተለያዩ ማህበራዊ ድጎማዎች ጉዳይ መስማማት አቅቷቸው መቆየታቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
አሁን ግን በህግ መወሰኛው ምክር ቤት /ሴኔት/ ዴሞክራቶቹ እንደራሴዎች በወጪ ዝርዝሩ ላይ መስማማታቸው ተሰምቷል፡፡
በበጀት እና በወጪ ዝርዝሩ ያለመፅደቅ የተነሳ ከ40 ቀናት በላይ መንግስታዊ አገልግሎቱ ተስተጓጉሎ መቆየቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
የአሁኑ የመንግስታዊ አገልግሎት መስተጓጎል የምንግዜውም ከፍተኛ እንደነበር ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡
ብሪታንያ የቤልጂየምን የአየር ክልል ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ ከጎንሽ ነኝ አለቻት፡፡
ብሪታንያ ቤልጂየምን በአየር ክልልሽን ለማስጠበቅ አግዣለሁ ያለቻት ዛቬንቴም በተሰኘው ኤርፖርቷ የአየር ክልል መነሻው በውል ያልተለየ ሰው አልባ በራሪ አካል /ድሮን/ ታይቷል መባሉን ተከትሎ እንደሆነ ዘ ኢንዲፔንደንት ፅፏል፡፡
አጋጣሚው ኤርፖርቱ በጊዜያዊት እንዲዘጋ አስገድዶ ነበር ተብሏል፡፡
መነሻው በውል ያልተየለው ድሮን የሩሲያ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡
ሩሲያ ግን ቀደም ሲል በዚህ ነገር እኔ በጭራሽ የለሁበትም ማለቷን መረጃው አስታውሷል፡፡
ብሪታንያ ግን የአየር መከላከያ ጠበብቶቿን ወደ ቤልጂየም መላኳ ታውቋል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments