top of page

ጳጉሜ 5 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Sep 10
  • 3 min read

የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰየሙ፡፡


በማክሮን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ሰቤስቲያን ሌኮርኑ እንደሆኑ AFP ፅፏል፡፡


ሌኮርኑ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እስከተሾሙ ድረስ የፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ቆይተዋል፡፡

ree

ቀዳሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንሷ ባይሩ የፓርላማውን የመተማመኛ ድምፅ በመንፈጋቸው ከትናንት በስቲያ የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡


ሌኮርኑ በፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የ8 አመታት አስተዳደር 7ኛው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡


በባይሩ እና በሌኮርኑ መካከል ዛሬ እኩለ ቀን ላይ የስልጣን እርክከብ እንደሚከናወን ታውቋል፡፡



የማሊ መንግስት ሰራዊት ካየስ በተባለው ግዛት በፅንፈኛ ታጣቂዎች ይዞታ ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት እየፈፀመ ነው ተባለ፡፡


በተለይም በምህፃሩ ጂኒም የተሰኘው ፅንፈኛ ቡድን በተለይም ወደ ርእሰ ከተማዋ ባማኮ ነዳጅ እንዳያልፍ መሰናክል እየፈጠረ ነው ተብሏል፡፡


በተለያዩ ማምረቻዎች እና የማዕድን ማውጫዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


ማሊ በአሁኑ ወቅት በሽግግር ወታደራዊ መንግስት እየተዳደረች ነው፡፡


ለአልቃይዳ እና ለIS ፅንፈኛ ቡድኖች ታማኝነታቸውን ያረጋገጡ ታጣቂዎች የአገሪቱ የደህንነት እና የፀጥታ ፈተናዎች ከሆኑ ቆይተዋል፡፡


እንደ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ያሉ የአቅራቢያው አገሮችም የተመሳሳይ ፈተና ተጋሪዎች እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡



አለም አቀፉ የወንጀል ችሎት /ICC/ በዩጋንዳው ሎርድስ ሬዚስታንስ አርሚ በተሰኘው አማጺ ቡድን መሪ ጆሴፍ ኮኒ ላይ የቀረበውን ክስ ማድመጥ ጀመረ፡፡


ችሎቱ በጆሴፍ ኮኒ ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ካወጣበት 20 አመታት ማስቆጠሩን GMA ኒውስ ፅፏል፡፡


ኮኒ ዩጋንዳን ለቅቆ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፖብሊክ ተሻግሯል ከተባለ ቆይቷል፡፡


ሆኖም ኮኒ በአሁኑ ወቅት ያለበት ትክክለኛ አድራሻ አይታወቅም፡፡


ችሎቱ የኮኒ ክስ በሌለበት እንዲታይ ከወሰነ 3 አመታት ሆኖታል፡፡


የጆሴፍ ኮኒ አማጺ ቡድን በሰሜናዊ ዩጋንዳ እና በኮንጎ ኪንሻሣ በብዙ ሺህዎች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ እልቂት ማድረሱ ይነገራል፡፡


እጅ እና እግር በመቆራረጥም ማሰቃየት ሲፈፅም ነበር ይባላል፡፡



የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሐማስ እስራኤል በካታር ዶሃ በፈፀመችው ድብደባ አምስት አባሎቼ ቢገደሉም መሪዎቼ ግን ከጥቃት ተርፈዋል አለ፡፡


የካታር የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አንድ የፀጥታ ባልደረባዬ በጥቃቱ ተገድሎብኛ ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በድብደባው በሐማስ ሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተጠቀሰው ነገር የለም፡፡


ካታር ባለፉት 13 አመታት የሐማስ ከፍተኛ መሪዎች መቀመጫ እንደሆነች በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


አሜሪካኖቹ ድብደባው ከመፈፀሙ አስቀድሞ ሰምተን ካታሮቹ እንዲያውቁት አድርገናል ብለዋል፡፡


ካታሮቹ ግን ደግሞ ከአሜሪካ በኩል ምንም የሰማነው ማስጠንቀቂያ የለም እያሉ ነው፡፡


እስራኤል በካታር የሐማሶች መኖሪያ ላይ አነጣጥራ የፈፀመችው ጥቃት ከካታር በተጨማሪ በሳውዲ አረቢያ ፣ በፈረንሳይ እና በተባበሩት መንግስት ድርጅት ዋና ፀሐፊ መወገዙ ተሰምቷል፡፡


የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪየር ስታርመር በበኩላቸው ነገሮችን ከማባባስ በጋዛ በአፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡



የካታር መንግስት እስራኤል በዶሃ በሚገኘው የሐማስ መሪዎች መኖሪያ ሕንፃ ላይ ጥቃት ማድረሷን አምርሮ አወገዘው፡፡


የካታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት የእስራኤልን እርምጃ በጭራሽ አንታገሰውም የሚል መግለጫ ማውጣቱን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


የእስራኤልን እርምጃም ሀላፊነት የጎደለው ነው ብሎታል፡፡


የካታር መንግስት ጉዳዩን ከስረ መሰረቱ እመረምረዋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር ትናት በዶሃ በሐማስ መሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሰንዘሩን እወቁልኝ ለማለት አላረፈደም፡፡


የሐማስን መሪዎች አሸባሪዎች ሲሉ የጠሩት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የቡድኑ መሪዎች የትም ይሁኑ የት ህጋዊ ዒላማዎቻችን ናቸው ብለዋል፡፡


ካታር በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለማስቻል ከአደራዳሪዎቹ አንዷ ሆና መቆየቷን መረጃው አስታውሷል፡፡



የሊባኖስ መንግስት ጦር ሔዝቦላህ የተሰኘውን ታጣቂ ቡድን በቅርቡ ትጥቅ ማስፈታት እንደሚጀምር የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሴፍ ራጊ ተናገሩ፡፡


ዮሴፍ ራጊ ሔዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታቱ በ5 ምዕራፎች ተከፋፍሎ ይከናወናል ማታቸውን ዘ ኒው አረብ ፅፏል፡፡


ቀዳሚው ትጥቅ ማስፈታት በተለይም በእስራኤል ወሰን አቅራቢያ እንደሚከናወን ራጊ ተናግረዋል፡፡


ይሄም በሚቀጥሉት 3 ወራት ይከናወናል ብለዋል ራጊ፡፡


በቀደመው ጊዜ ተፈሪ እና ገናና የነበረው ሔዝቦላህ ቀደም ሲል ከእስራኤል ጋር ለአመት ያህል በተካሄደው ጦርነት መዳከሙ ይነገራል፡፡


በጦርነቱ እንደ ሐሰን ናስረላህ ያሉ ስመ ጥር መሪዎቹን አጥቷል፡፡


ሔዝቦላህ በአሁኑ ወቅት እጅግ በተዳከመ አቅሙ ላይ ይገኛል ቢባልም በጭራሽ ትጥቅ አልፈታም እያለ ነው፡፡


ሔዝቦላህ የእስራኤል ዋነኛዋ ጠላት ተደርጋ የምትቆጠረው ኢራን የጦር እና የፖለቲካ ሸሪክ ሆኖ መቆየቱን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page