top of page

ጥቅምት 4 2018 - የንጋት ሃይቅ ሳይበከልና በደለል ሳይጎዳ እንዲቀጥል የማድረግ ሰራ መሰራት አለበት ተባለ።

  • sheger1021fm
  • Oct 14
  • 2 min read

የንጋት ሃይቅን ከአደጋ የሚጠብቅ በዙሪያው የሚሰራው ስራም በጥናት የተደገፈና የተናበበ እንዲሆን ያደርጋል የተባለለት ፍኖተ ካርታ እየተሰናዳለት ነው።


ኢትዮጵያ ከ #ንጋት_ሀይቅ በሚገባት ልክ መጠቀም ያለባት እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ ፍኖተ ካርታው መልስ ይሰጣል ብለዋል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ፡፡


ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል፣ የንጋት ሃይቅም ይመራበታል የተባለ የንጋት ሃይቅና አካባቢው የተቀናጀ ፍኖተ ካርታ ተሰናድቶ ምክክር እየተደረገበት ነው።


የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለቤት ሆኖ ያሰራው ረቂቅ ፍኖተ ካርታ በኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን መሰራቱ ተነግሯል።


የንጋት ሃይቅ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተጠናቅቆ ይፋ ሲሆን ከዚህ በኋላ በውሃ ሀብቱ ዙሪያ ምን ይሰራ ለሚለው መልስ ይሰጣል ተብሏል።


የህዳሴውን ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ ከውሃው የኤሌክትሪክ ሀይል ከማመንጨት ባለፈ ከዚህ የውሃ ሀብት በተገቢው መንገድ መጠቀም ያለብን እንዴት ነው ለሚለው መልስ መስጠት ያስፈልጋል ተብሏል።


የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ፣ የህዳሴውን ግድብ መገንባት ተከትሎ የተፈጠረው ንጋት ሰው ሰራሽ ሃይቅ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃን የያዘና፣ ሽፋኑም ከ240 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም መሆኑን አንስተዋል።


በውስጡም ከ70 በላይ ደሴቶችን ከያዘው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ኢትዮጵያ በልኩ መጠቀም እንዳለባት አንስተዋል።

ree

ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ሲሰናዳ ነበር፣ የህዳሴውን ግድብ መጠናቀቅ ተከትሎም ይፋ ተደርጓል የተባለው ረቂቅ ፍኖተ ካርታው የሰው ሰራሽ ሃይቁንና በዙሪያው ያለውን ሀብት እንዴት እንጠቀምበት ለሚለው ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል።


የንጋት ሃይቅ ከውሃ ትራንስፖርት፣ መስኖ፣ ግብርና፣ የዓሳ ሀብት፣ ቱሪዝም እና ሌሎችም ዘርፎች ጋር የሚገናኝ ስለሆነ በረቂቅ ደረጃ የተሰናዳው ፍኖተ ካርታም ሁሉንም ታሳቢ አድርጎ የተሰናዳ ነው ተብሏል።


በውሃው ዙሪያ ያለውን ጥብቅ ቦታ(Buffer zone) በጥናት ላይ ተመስርቶ መለየትም አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ  ተናግረዋል።


የቀረበው ረቂቅ ከያዛቸው ዝርዝር ነጥቦች ውስጥ ለግድቡና ለውሃ ሀብቱ ደህንነት ሲባል የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መሰራት ያለባቸው ስራዎች ተዘርዝረዋል።


የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣በውሃው ዙሪያ ካለ እርሻ ታጥቦ ወደ ሀይቁ የሚገባ ኬሚካል ውሃውን እንዳይበክል መጠበቅ፣ደለልን በመከላከልና ሌሎችም መሰራት ያለባቸው ነጥቦች በዝርዝር ቀርቦበታል።


የንጋት ሃይቅን መፈጠር ተከትሎም በዙሪያው የሚሰራው ስራ ምን መሆን አለበት የሚለውም በደንብ መጠናት አለበት ተብሏል።


ቱሪዝምን በተመለከተ በውሃው ዙሪያ የት ምን መሰራት አለበት ከሚለው አንስቶ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች የውሃና የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት በምን መሸፈን አለበት የሚለው ሁሉ በጥናት ይለያል ተብሏል።


አሁን የህዳሴው ግድብ የያዘው 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ባለበት መቀጠሉን በየጊዜው በሳይንሳዊ መንገድ በመለካት ማወቅ ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን ለዚህም በተለዩ ቦታዎች ላይ መቆጣጠሪያ ጌጆችን መትከል፣እንዲሁም የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያዎችን በዙሪያው ማብዛት እንደሚያስፈልግ ተነግሯል።


ዛሬ በመነሻ ደረጃ የቀረበው ጥናት ተጨማሪ ምክክር እና ዝግጅት ተደርጎበት ገዢ ፍኖተ ካርታ ሆኖ ይወጣል ተብሏል።


ከዛ በውሃላ በተፋሰሱ ዙሪያ ለሚሰሩ ፕሮጀክቶች መነሻም ማመሳከሪያም ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።


ቴዎድሮስ ወርቁ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page