ጥቅምት 27 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 5 minutes ago
- 2 min read
ፊሊፒንስን ሰሞኑን በመታት ከባድ አውሎ ነፋስ የሟቾቹ ብዛት ከ140 በላይ መድረሱ ተሰማ፡፡
አውሎ ነፋሱ በከባድ ጎርፍ እና በመሬት መንሸራተት ጭምር የታገዘ እንደነበር AFP አስታውሷል፡፡
በአደጋው ከሞቱት እና አካላዊ ጉዳት ከገጠማቸው ሌላ 127 ሰዎች ደግሞ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል፡፡
ይህም የሟቾቹ ብዛት ከተጠቀሰውም በላይ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡

ሴቡ የተባለችዋ ግዛት ዋነኛዋ የአደጋው ሰለባ ነች፡፡
በግዛቲቱ የደረሰው ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ከዚህ ቀደም ከደረሱት ሁሉ በእጅጉ ከባድ ነበር ተብሏል፡፡
ጎርፉ መኪኖችን እና ትልልቅ ኮንቴይነሮችን ጭምር አንከብክቦ መጋለቡ ታውቋል፡፡
ለፊሊፒንሱ አውሎ ነፋስ ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ የአየር ለውጡ በዋና ምክንያትነት እየቀረበ ነው፡፡
የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬይን ፖክሮቭስክ ከተማ ይዞታዬን እያጠናከርኩ ነው አለ፡፡
የሩሲያ ጦር የከተማዋን ሰሜናዊ ክፍል ከዩክሬይን ወታደሮች እያፀዳሁ ነው ማለቱን ሬውተርስ ፅፏል፡፡
ፖክሮቭስክ ለዩክሬይን ጦር ዋነኛዋ የስንቅ እና ትጥቅ ማጓጓዣ መስመር ሆና ቆይታለች፡፡
ወታደራዊ ፋይዳዋም የጎላ መሆኑ ይነገራል፡፡
የሩሲያ ጦር ፖክሮቭስክን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ በዳኔስክ ግዛት ይገባኛል የሚለውን ቀሪ 10 በመቶ ግዛት ለመያዝ ያግዘዋል ተብሏል፡፡
የሩሲያ ጦር በፖክሮቭስክ ጥቃቴን አጠናክሬያለሁ ስለማለቱ ከዩክሬይን ሰራዊት በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡
የሩሲያ እና የዩክሬይን ጦርነት ያለ ሁነኛ መፍትሄ 3 አመት ከመንፈቅ ሆኖታል፡፡
የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን በጋዛ የፀጥታ ቁጥጥሩን የፍልስጤም አስተዳደር እንዲረከበው ተስማምቻለሁ አለ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ያቀረቡት ባለ 20 ነጥቦች የሰላም እቅድ ደግሞ በጋዛ የደህንነት ሁኔታው ቁጥጥር በአለም አቀፍ አረጋጊ ሀይል እንዲከወን የሚጠይቅ መሆኑን ሚድል ኢስት ሞኒተር አስታውሷል፡፡
የሐማስ ከፍተኛ ሹም የሆኑት አቡ ማርዙክ አለም አቀፍ ሀይል እንዲሰማራ ከተፈለገ የፀጥታው ምክር ቤት ይሁንታ እና ድጋፍ እንደሚያሻው ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ እና እስራኤል ደግሞ አረጋጊው ሀይል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስራ እንዲሆን አይፈልጉም ብለዋል፡፡
በትራምፕ እቅድ ላይ በሰፈረው መሰረት የሐማስ ትጥቅ መፍታትም ሆነ የአለም አቀፉ አረጋጊ ሀይል የጋዛ ስምሪት በቀጣዩ ምዕራፍ ድርድር የሚታይ ጉዳይ መሆኑ ይነገራል፡፡
ጉዳዩ ግን ያገባናል ባይ ወገኖችን ከወዲሁ እያወዛገበ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
አለም አቀፉ የአቶሚክ ሀይል ተቆጣጣሪ ድርጅት (IAEA) ኢራን ለድርጅቱ ቁጥጥር ብትተባበር ይሻላታል አለ፡፡
ኢራን በኒኩሊየር መርሐ ግብሯ የተነሳ ከምዕራባዊያኑ ኃያላን ጋር ውዝግቧ ዳግም እየተጋጋለ መምጣቱን ዘ ኒው አረብ ፅፏል፡፡
ምዕራባዊያ ኃያላን ኢራን የኒኩሊየር ቦምብ የመስራት ፍላጎት አላት ሲሉ በተደጋጋሚ እየከሰሷት ነው፡፡
ቴሕራን ግን የኒኩሊየር መርሐ ግብሬ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እና ለሰላማዊ አገልግሎቶች የታለመ ነው ስትል ትሟገታለች፡፡
አሁን አሁን ምዕራባዊያኑ ኃያላን ኢራን በማንኛውም ሁኔታ ዩራኒየም ማብላላቷን ከነጭራሹ ማቆም አለባት የሚል አቋም እየያዙ ነው፡፡
ኢራን ከምዕራባዊያኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአለም አቀፉ ተቆጣጣሪ አካል ጋርም ግንኙነቷ በእጅጉ እየሻከረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








