የባቱ - አርሲ ነገሌ 57 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎቹ ተጠናቅቀዋል ተባለ።
- 2 hours ago
- 2 min read
የካቲት 26/2018
የሞጆ - ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ አካል የሆነው የባቱ - አርሲ ነገሌ 57 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ግንባታ ዋና ዋና ሥራዎቹ ተጠናቅቀዋል ተባለ።
የመንገድ ኮሪደሩ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ አርሲ ዞኖች የሚገኙትን የባቱ ከተማን፣ የአዳሚ ቱሉ እና አርሲ ነገሌ ወረዳዎችን ጨምሮ ከ17 በላይ ቀበሌዎችን ያስተሳስራል ተብሏል።
የመንገድ ግንባታው የአዲስ አበባ - ሞያሌ - ናይሮቢ - ሞምባሳ የመንገድ ኮሪደር አካል መሆኑ ተነግሯል።
ግንባታውን ለማከናወን ከዓለም ባንክ የተገኘ 5.3 ቢሊዮን ብር ወጪ መሆኑ ተነግሯል።
57 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የባቱ - አርሲ ነገሌ የፍጥነት መንገድ ግንባታ በ90 ሜትር የመንገድ ወሰን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ የጎን ስፋቱ የመንገድ አካፋይን ጨምሮ 31.6 ሜትር መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ተናግሯል።
መንገዱ ሙሉ በሙሉ ከከተማ ውጪ የሚያልፍና ከከተማዎች ጋር የሚያስተሳስሩ አገናኝ መንገዶች ያሉት ነው ተብሏል።
አገናኝ መንገዶቹ በገጠር 10 ሜትር፣ በከተማ ደግሞ 22.5 ሜትር የጎን ስፋት እንዳላቸውም ተናግሯል።
የግንባታ ሥራውን ዓለም አቀፉ የቻይና የሥራ ተቋራጭ፣ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ መስራቱንም ተቋሙ ካወጣው መረጃ ተመልክተናል።
ኩንሃ ኢንጂነሪንግ እና ኮንሰልቲንግ ከኮሪያ ኤክስፕረስዌይ ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር፣ እንዲሁም ሀገር በቀሉ ንዑስ አማካሪ፣ኢትዮ ኢንፍራ ኢንጂነሪንግ ኃ.የተ.የግ.ኩባንያ የማማከሩንና የቁጥጥሩን ሥራ በጋራ ሰርተዋልም ተብሏል።

መንገዱ የአዲስ አበባ - ሞጆ - ሞያሌ - ላሙ - ሞምባሳ ትራንስ ኢንተርናሽናል ሐይዌይ እንዲሁም 10,000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ኮሪደር (ኬፕታውን ትራንስ አፍሪካን ሐይዌይ) አካል መሆኑን የጠቀሰው ተቋሙ በጎረቤት ሀገራት መሀከል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ብሏል።
የንግድ እና የቱሪዝም ፍሰትን ለማቀላጠፍ ያግዛል የተባለው መንገዱ የእርሻና ኢንዱስትሪ ማዕከላትን እንዲሁም የቱሪስት መስህቦችን ለማገናኘት የሚያስችል ነውም ተብሏል።
የሀሮ ደምበል፣ ላንጋኖ፣ አብያታ እና ሻላ ሐይቆችን እንዲሁም ሐዋሳን ለመጎብኘት ለሚያስቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ጉዞን ያቀላልም ብሏል።
ፕሮጀክቱ ከሞጆ - ሐዋሳ የነበረውን የ4 ሰዓት የጉዞ ጊዜ ወደ 2 ሰዓት ዝቅ እንደሚያደርግም ተነግሯል።
በተጨማሪም በአካባቢው በስፋት የሚመረተው እንደ ስንዴ፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ፓፓያ እና ድንች ያሉ የግብርና ምርቶች ሳይዘገዩ በፍጥነት ለገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግም ወሳኝ ነው ተብሏል።
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
X :- https://x.com/shegerfm?s=2
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments