ጥቅምት 14 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 2 hours ago
- 2 min read
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአሜሪካም ሆነ ለሌሎች አገሮች ጫና በጭራሽ አንበገርም አሉ፡፡
የፑቲን አስተያየት የተሰማው አሜሪካ በሁለት ታላላቅ የሩሲያ የነዳጅ ኩባንያዎች ላይ ማእቀብ መጣሏን ተከትሎ እንደሆነ ዘ ስትሪይትስ ታይምስ ፅፏል፡፡
አሜሪካ በሩሲያ የነዳጅ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ የጣለችው የዩክሬይኑን ጦርነት ለማስቆም በሞስኮ ላይ ጫና ለመፍጠር አልማ ነው ተብሏል፡፡

ፑቲን የአሜሪካን የማዕቀብ እርምጃ ገንቢ ያልሆነ ብለውታል፡፡
አገራቸው ለዚህ እና ለሌሎችም ጫናዎች እንደማትበገር የሩሲያው ፕሬዘዳንት ተናግረዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት አሜሪካ ለዩክሬይን ቶም ሐውክ የተባለውን የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየል እንዳታስታጥቅ በብርቱ አስጠንቅቀዋል፡፡
ሆኖም በዚህ ዓይነት የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ላይ ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ ውርድ ከራሴ ማለታቸው ተሰምቷል ፑቲን፡፡
የእስራኤል ጦር በሊባኖስ በሔዝቦላህ ታጣቂ ቡድን ይዞታ ላይ ከባድ የአየር ድብደባ እየፈፀመ ነው ተባለ፡፡
ጦሩም ድብደባውን እየፈፀመ ስለመሆኑ ማረጋገጫ መስጠቱን ዘ ኒው አረብ ፅፏል፡፡
የእስራኤል ጦር በሔዝቦላህ ይዞታዎች ላይ ድብደባውን የሚፈፅመው ሊባኖስ ከሶሪያ በምትዋሰንበት ምስራቃዊው የቤካ ግዛት መሆኑ ታውቋል፡፡
የሔዝቦላህ የጦር ሰፈሮች እና የሚሳየል ማምረቻዎች የእስራኤል ጦር ዒላማዎች ናቸው ተብሏል፡፡
ከአመት ገደማ በፊት የተኩስ አቁም ቢደረስም እስራኤል አሁንም ድረስ ሊባኖስ ውስጥ ጥቃት ማድረሷን እንደቀጠለች ይነገራል፡፡
ከአሜሪካ በደረሰበት ግፊት ምክንያት የሊባኖስ መንግስት ሔዝቦላህን ትጥቅ አስፈታለሁ ካለ ቆይቷል፡፡
ሆኖም ሄዝቦላህ ትጥቅ አልፈታም ብሎ እያንገራገረ ነው ይባላል፡፡
ሔዝቦላህ የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ ሸሪክ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የናይጀርያ ጦር በፅንፈኞች የጦር ሰፈሮች ላይ ባደረስኩት የተቀናጀ ጥቃት 50 ታጣቂዎችን ገደልኩ አለ፡፡
ፅንፈኛ ታጣቂዎቹ በጦሩ የተገደሉ በቦርኖ እና ዮቤ ግዛቶች የተለያዩ ስፍራዎች እንደሆነ AFP ፅፏል፡፡
ጦሩ ከእግረኛ ሀይል በተጨማሪ አጥቂ ሰው አልባ በራሪ አካላት /ድሮኖችንም/ ጥቅም ላይ ማዋሉ ታውቋል፡፡
የናይጀሪያ ጦር እንደ በኮ ሐራም እና ከቀጠናው የIS ፅንፈኛ ቡድን ተቀጥላዎች ጋር ሲዋጋ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ፅንፈኛ ታጣቂዎች አሁንም ድረስ የናይጀሪያ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ሆነው መቀጠላቸው ይነገራል፡፡
በፅንፈኞቹ ጥቃት ከ40,000 የማያንሱ ሰዎች ሲገደሉ ፤ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ መረጃው አስታውሷል፡፡
የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ (ሳድክ) የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን የታንዛኒያው የምርጫ ሒደት እና ክንውን የሰመረ እንዲሆን ጠየቀ፡፡
የታዛቢዎቹ ቡድን ምርጫው የዴሞክራሲ እሴቶችን እና መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ መከናወን ይጠበቅበታል ማለቱን ዘ ኢስት አፍሪካን ፅፏል፡፡
በታንዛኒያ በመጪው ሳምንት ረቡዕ ፕሬዘዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫዎች ይደረጋሉ፡፡
የሳድክ ታዛቢ ቡድን ወደ ታንዛኒያ ከገባ መሰንበቱ ታውቋል፡፡
የአሁኑ ምርጫ የሚካሄደው የዋነኛው ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር ቻዴማ መሪ ቱንዱ ሊሱ እና ምክትላቸው በእስር ላይ በሚገኙበት ወቅት ነው፡፡
ቻዴማ የምርጫውን የሥነ ምግባር ደምብ አልፈረመም ተብሎ በምርጫው እንዳይፎካከር ተከልክሏል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








