ጥቅምት 14 2018 - የባዮቴክኖሎጂ ውጤት የሆነው የዘረመል ምህድስና GMO
- sheger1021fm
- 7 hours ago
- 3 min read
ኢትዮጵያ ግብርናን ቀድመው ከጀመሩ የዓለም ሀገራት ስሟ ቀድሞ ይነሳል፡፡
ዛሬም ግን ሀገሪቱ የትናንት የሚባል ታሪክ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንኳን በምግብ እራሷን ችላ መሰለፍ ተስኗታል፡፡
በ21ኛው ከፍለ ዘመንም የርሃብ፣ የምግብ እጦት፣ ዜና ከምድሯ አልጠፋም፡፡
ከ1,600 በላይ ዝርያዎችን ባለፉት 70 ዓመታት ለአርሶ አደሮች ማከፋፈሉን የሚናገሩት የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር)፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር በጣም እየጨመረ መሆኑን አስረድተው፤ የሰብል ምርቶች ምርታማነትም በእጥፍ መጨመሩን አብራርተዋል፡፡
ለምሳሌ በአርሶ አደር ማሳ ላይ ጤፍ በሄክታር ከ10 ኩንታል ወደ 20፣ ስንዴ ከ20 ወደ 36፣ ቦሎቄ ከ14 ወደ 28 ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡

ንጉሴ ደቻሳ(ፕ/ር) ይህም ሆኖ የምርት እድገቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት መጨመር ጋር እኩል መሆን እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ቁልፍ ጉዳይ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ማሳካት የሚቻለው ደግሞ የግብርናውን መስክ ሊለውጡ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማምጣት ሲቻል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የባዮቴክኖሎጂ ውጤት የሆነው #የዘረመል_ምህድስና (GMO) ነው፡፡ ይህን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በማምጣት እና ወደ ስራ በማስገባት በአንድ እና በሁለት ሳይሆን በሶስት እና በአራት እጥፍ ምርት የመጨመር ስራ መስራት ግዴታ ነው ይላሉ፡፡
የሀገሪቱ ህዝብ በጣም እየጨመረ ነው፤ ኢኮኖሚውም እያደገ ነው ስለዚህ ሁለቱንም ሊሸከም የሚችል ግብርናን መፍጠር ደግሞ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) ድርቅ ፣ ተባይ፣ የአፈር ለምነት መሟጠጥ፣ የገበያ ትስስር ማጣት እና ሌሎች ደግሞ የአርሶ አደሩ መሰረታዊ እና ያልተፈቱ ችግሮች እንደሆኑ ዘርዝረዋል፡፡

ቴላ ሜዝ በተሰኘ ፕሮጀክት በመልካሳ የግብርና ምርምር በባዮቴክ የለማው BT Maize የበቆሎ ዝርያ ደግሞ እነዚህ ችግሮች ተቋቁሞ ለአርሶ አደሩ የጉልበቱን ልፋት የሚከፍል፣ ምርትን የሚጨምር፣ ለኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት ኢንዲቀርብ የሚያስችል፣ ለሀገሩ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጪ ምርት እድገት ከፍተኛ ድርሻ የሚኖረው ምርት መመረቱን ሰምተናል፡፡
የዝርያው ተባይን መቋቋም አቅም ደግሞ አርሶ አደሩ ለተባይ ማጥፊያ ኬሚካል መግዣ የሚያወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን የአካባቢን ብከለትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከግብርና ባለስልጣን፣ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከአካባቢ ጥበቃ በለስልጣን የተወጣጣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በቴክኖሎጂው በኦሮሚያ ክልል መልካሳ የግብርና ምርምር የለማውን ቦቆሎ ዝርያ በጎበኙበት ወቅት ተነግሯል፡፡
በስፍራው ላይ ስለ ባዮቴክኖሎጂው እና ስለ በቆሎ ዝርያው ማብራርያ የሰጡት የግብርና ተመራማሪው እና በኢትዮጵያ የባዮ ቴክኖሎጂ ማህበረሰብ (Biotechnology society of Ethiopia) ፕሬዝዳንት ፍሬው መክብብ (ፕ/ር) ኢትዮጵያ ታላቅ ህዝብ እና ታላቅ ታሪክ ያላት ሀገር ነች ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይህን ታላቅነት ግን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ካልታገዘ የትም አንደረስም ሲሉ ተናግረው በዚህ ላይ ኢንቨስት እያደረግን ነው፤ ኢንቨስት የምናደርገው ግን ስለተረፈን ሳይሆን እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡
ወደፊት አለምን የሚመሩ ሁለት ትልልቅ መስኮች አሉ አንደኛው ኤአይ(AI) ነው ሁለተኛው ደግሞ ባዮ ቴክኖሎጂ ነው ፤ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ቀድሞ የሄደ ሀገር አለምን ይቆጣጠራል ሲሉ አሰረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ድሪባ ኩማ አዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ በቀድሞ ላይ በተመረኮዘው የአገሬው ሰው እና ቴክኖሎጂው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በሚፈልጉ ሰዎች መካከል የጥቅም ግጭት ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ቴክኖሎጂውን የሚቃወሙ አካላት አንዳሉ የዘረዘሩት አቶ ደሪባ፤ ለምሳሌ ነባሩ ላይ ተመስርተው ዘር የሚያቀርቡ እና የኢኮኖሚ ትስስር ያላቸው አካላት እንዲሁም የጸረ ተባይ ኬሚካል የሚያቀርቡ መንግስታዊው ያልሆኑ ድርጅቶች ወይም ተቋማት ስላሉ እነሱ የባዮ ቴክኖሎጂውን ላይደግፉት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ይህን መሰል ዝርያዎች ያለ ኬሚካል ተባይን መቋቋም ስለሚችሉ የገበያ እና የጥቅም ትስርስርን ስለሚያስቀር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በቴክኖሎጂው ላይ ችግሮች ካሉ በሳይንሳዊ መንገድ መፈተሽ እና መስተካካል ይቻላል ያሉት ዳይሬክተሩ የጥቅም ግጭትን ግን መከላከል ያስፈልጋል ምክንያቱም ደግሞ ሳይንሳዊ ሳይሆን ፖለቲካ ስለሆነ ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) ባዮቴክኖሎጂውን የሚቃወሙትንም ሆነ የሚደገፉት ለሀገር እንደሆነ ተናግረው የሚበጀው የትኛው ነው የሚለውን ማየት እና መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አንድ ቴክኖሎጂ ሲመጣ የምግብ ደህነንትን ማረጋገጡን፣ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ላይ በአይነት እና በመጠን ይጨምራል ወይ ፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን ያሳድጋል ወይ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ለምግብ የሚገቡ ግብዓቶችን ማስቀረቱን እና የስራ እድል ላይ ምን ይጨምራል የሚለውን ማየት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት መለስ መኮንን (ዶ/ር) መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የግብርና ምርምር ኢንትስቲትዩ ይህ የበቆሎ ዝርያ ለሁሉም አርሶ አደሮች እንዲደርስ አርሶ አደሩም የተሻለ እንዲያመርተው የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሙሉ ፍቃድ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
ምክንያቱ ደግሞ በዘረመል ምህድስና ዝርያዎች ሲመጡ የስነ ሕይወታዊ ደህንንት ማረጋገጫ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ ይህንን የሚሠጠው ደግሞ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ነው፡፡
ይሀንን ማረጋገጫ የሚሰጠው የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ያቀረበው ማመልከቻው እየታያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቴክኖሎጂው ታይቶ ሀገርን እና አርሶ አደሩን የሚጠቅም እንዲሁም አካባቢን የማይጎዳ ከሆነ እንደሚፈቅድ ተናግረዋል፡፡
BT Maize የበቆሎ ዝርያ ለኢትዮጵያ አርሶ አደር ፈተና የሆኑ ድርቅን እና ተባይን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ……
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments