ጥቅምት 12 2018 - አሲዳማ መሬትን ለማከም የሚረዳ የኖራ ወፍጮ በተለያዩ ክልሎች ሊያቋቁም መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ተናገረ
- sheger1021fm
- 1 hour ago
- 1 min read
በአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ እርዳታ አሲዳማ መሬትን ለማከም የሚረዳ የኖራ ወፍጮ በተለያዩ ክልሎች ሊያቋቁም መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ተናገረ፡፡
ለዚህ ተግባር የሚውል የ20 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ከአለም ባንክ መገኘቱም ተሰምቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከምታርሰው መሬት ውስጥ 43 ከመቶ ወይም 7 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬቷ በአሲድ እንደተጠቃ የግብርና ሚኒስቴር ከአንድ ዓመት በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡
3.1 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው ደግሞ በጠንካራ አሲድ የተጠቃ አፈር ነው ተብሏል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤሊያስ (ፕ/ር) በአሲድ የተጠቃው መሬት ምርትን ከ70 እስከ 100 በመቶ ምርት እንደሚቀንስ ተናግረው ይህም የሀገሪቱን የግብርና ስራ ፈታኝ አድርጎታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኢሲድ የተጠቃው መሬት ከፍተኛ ዝናብ እና እርጥበት ያለበት አካባቢ መሆኑ ደግሞ ግብርናውን ጎድቶታል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤሊያስ ጠቁመዋል፡፡
በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል ማለትም ከምዕራብ አማራ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ ያለው መሬት በሙሉ በአሲድ የተጠቃ ነው ተብሏል፡፡
ይህን መሬት ለማከም ደግሞ ፈተና የሆነው የኖራ አቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ነው ያሉት እያሱ ኤሊያስ (ፕ/ር) ኖራው ያለው በምዕራቡ የሀገሪቱ ከፍል ስለሆነ የተፈጨ የኖራ ድንጋይ ሩቅ መንገድ በተሽከርካሪ ማጓጓዝ ከባድ ሆኖብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ከአጋር አካላት ትብብር እየፈለግን ነው ዘንድሮም ከዓለም ባንክ 20 ሚሊዮን ዶላር አግኝተናል ብለዋል የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው፡፡
በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የኖራ ወፍጮ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሯል ሲሉ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤሊያስ (ፕ/ር) አስረድተዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s