ጥር 27/2018 – የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- 3 minutes ago
- 2 min read
የሱዳን ወታደራዊ መንግስት እና የአገሪቱ ጦር የበላይ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የአገሪቱ ጦር የደቡብ ኮርዶፋኗን ዋና ከተማ ካዱግሊን ከተቀሩት ክፍሎች ጋር የሚያገናኘውን አውራ ጎዳና በእጁ ማስገባቱን ተናገሩ፡፡
ጦሩ የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል በካዱግሊ ፈጥሮት የነበረውን ከበባ ጥሶ እንደወጣ አል ቡርሃን መናገራቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
አብዱልፈታህ አልቡርሃን የደቡብ ኮርዳፋኗን ከተማ ከተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ጋር የሚያገናኘውን አውራ ጎዳና ተቆጣጥረነዋል ያሉት በኦምዱርማን በሚገኘው የአገሪቱ ዋና የቴሌቪዥን ጣቢያ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው ተብሏል፡፡

ጄኔራል አል ቡርሃን ከRSF ጋር በጭራሽ የተኩስ አቁም አናደርግም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ የተኩስ አቁም RSF መልሶ እንዲያንሰራራ ስለሚያደርገው በጭራሽ በተኩስ አቁም እንደማይስማሙ ተናግረዋል፡፡
የሱዳኑ ጦርነት ያለ ሁነኛ መፍትሄ ወደ 3ኛ አመቱ እየተቃረበ መምጣቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
በኬንያ ባለ ዝቅተኛ ገቢ ዜጎች ከገቢ ግብር ነፃ ሊደረጉ ነው፡፡
ወርሃዊ ገቢያቸው 30 ሺህ ሺልንግ እና ከዚያ በታች የሆነ ኬኒያውያን ከገቢ ግብር ነፃ እንደሚሆኑ የገንዘብ ሚኒስትሩ ጆን ምባዲ መናገራቸውን TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡
እርምጃው በአገሪቱ ባለ ዝቅተኛ ገቢዎቹን የኑሮ ጫና ለማቅለል የታለመ ነው ተብሏል፡፡
30 ሺህ ሺልንግ የ235 ዶላር የምንዛሪ ግምት እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
30 ሺህ ሺልንግ እና ከዚያ በታች ወርሃዊ ገቢ ያላቸው ከማንኛውም የገቢ ግብር ነፃ መደረጋቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኬኒያውያንን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
ከ2 ዓመታት በፊት ታስቦ የነበረው የግብር ጭማሪ ግጭት ያስከተለ ተቃውሞ ቀስቅሶ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡
ስፔንም እድሜያቸው ከ16 አመት በታች የሆነ አዳጊ ወጣቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዳይገለገሉ ልታደርግ ነው፡፡
አውስትራሊያ ቀደም ሲል አዳጊ ወጣቶችን እንደ ቲክ ቶክ፣ ፌስ ቡክ ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን እንዳይገለገሉ የሚያደርግ ህግ ስራ ላይ ማዋሏን አረብ ኒውስ አስታውሷል፡፡
የፈረንሳይ ፓርላማም ባለፈው ሳምንት እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆነ አዳጊዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ እንዳይገለገሉ የሚያደርግ ህግ አፅድቋል፡፡
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ አገራቸውም ይሄንኑ ፈለግ እንደምትከተል ተናግረዋል፡፡
እርምጃው የአገሪቱን አዳጊዎች ከተለያዩ ማህበራዊ ጠንቆች ለመጠበቅ የታለመ ነው ተብሏል፡፡
ጉዳዩ በብዙ አገሮች ከዋና ዋና መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ








