top of page

ጥር 17፣ 2015- ኢትዮጵያ የሚበላ ምግብ ዋጋ ውድ ከሆነባቸው የአፍሪካ ሃገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ነች ተባለ


ኢትዮጵያ የሚበላ ምግብ ዋጋ ውድ ከሆነባቸው የአፍሪካ ሃገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ነች ተባለ፡፡


ከአለም 8ተኛ ደረጃ ላይ መሆኗን ሰምተናል፡፡


ከዚምባቡዌ ቀጥላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያለባት ሃገር እንደሆነች በጥናት ተረጋግጧል፡፡


የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በዋጋ ግሸበት ምክንያቶችና መፍትሄ ላይ ያደረገውን ጥናት ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ይፋ አድርጓል፡፡


አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 49.1 በመቶ ነው የተባለ ሲሆን የምግብ የዋጋ ንረት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡


ይህም ከክልል ክልል የተለያየ መሆኑ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡


በአማራና ደቡብ ክልል ያለው የዋጋ ግሽበት ከሃገራዊ ምጣኔው ከፍ ያለ ነው ተብሏል፡፡


በተለይ ለምግብ የዋጋ ንረቱ የምርት መጠን ከፍላጎት ጋር አለመመጣጠን አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል ጥናቱን ያቀረቡት ዶ/ር ታደሰ ኩማ፡፡


ገበሬው ከሚያመርተው ምርት ከራሱ ፍጆታ ተርፎት ለገበያ የሚያቀርበው በአማካይ ከ20 በመቶ አይበልጥም ተብሏል፡፡


ከሚመረተው በቆሎ 85 በመቶው ገበሬው ለእለት ፍጆታው ያውለዋል ተብሏል፡፡


በሌላ በኩል ከሚመረተው ጤፍ ለገበያ ቀርቦ ከተማው የሚሸምተው 30 በመቶውን ብቻ ነው ተብሏል፡፡


ይህም ምርታማነት ጨምሯል ቢባልም አብዛኛው አነስተኛ አምራች ገበሬ በመሆኑ የሚያመርተው እህል እምብዛም ከራሱ የሚያልፍ በመሆኑ ዋጋ እንዲንር ምክንያት መሆኑን ሰምተናል፡፡


ማምረት እንደተቻለ ከውጭ ማስመጣት ደግሞ ሌላው ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡


ኢትዮጵያ ከ97 በመቶ በላይ የዘይት ፍላጎቷን ከውጭ ገዝታ እንደምታመጣም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡


ከፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ባሻገር እሴት የማይጨምሩ ደላሎች በገበያ ሰንሰለቱ በብዛት መሳተፍ ፣ መንግስትም ተገቢውን ቁጥጥርና የእርምት እርምጃ አለመውሰድ የዋጋ ንረቱን አባብሶታል ይላል ጥናቱ፡፡


በዚህም ምክንያት ምርት አምራቹ ከሚሸጥበት 58 በመቶ ዋጋው ከፍ ብሎ ሸማቹ ጋር እንዲደርስ አድርጓል ተብሏል፡፡


ይህን ሁኔታ ለመቀየር መንግስት የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ ጥናቱ መክሯል፡፡


ገበያውን ማዘመን፣ የገበያውን ምርታማነት ለመጨመር ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡


በተጨማሪም የተቋማት አደረጃጀትና አሰራርን በመፈተሽ ተገቢውን እና መልክ ያጣውን የገበያ ሥርዓት ማስተካልም የመንግስት የቤት ስራ ነው ተብሏል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን


ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


bottom of page