ህዳር 25 2018 በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ወስደው ሰፈራ መሬት ከወሰዱ ባለሀብቶች እስከ 75 በመቶው ወደ ልማት ሲገቡ አይታይም፡፡
- sheger1021fm
- 25 minutes ago
- 2 min read

መሬቱ ላይ ለመስራት ሳይሆን በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ፈቃድ የባንክ ብድር ለማግኘት አልመው ወደዚህ ስራ የሚገቡ አሉ ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ 7,000 የሚሆኑ ባለሃብቶች በእርሻ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት 2.2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያዩ ክልሎች መውሰዳቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
ባለሃብቶቹ መሬቱን የወሰዱት ለገበያ የሚውሉ የተለያዩ ሰብሎችን ለማምረት እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።
ለግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰጠው 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት እስከ አሁን ባለሃብቶቹ የለማው ግን 25 በመቶው ብቻ እንደሆነ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ ተናግረዋል።
የለማው 25 በመቶ መሬትም ቢሆን ምርታማነቱ አጥጋቢ እንዳልሆነ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፤
የመስሪያ ቤታቸውን የ2018 በጀት አመት የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ጠቅሰዋል።
ባለሃብቶች በሚጠበቀው ልክ የወሰዱትን መሬት ያላለሙባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ ያሉን በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ አበበ ናቸው።
የመጀመሪያው መሬቱ ላይ ለመስራት ሳይሆን የተሰጣቸውን የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተጠቅመው ከባንክ ብድር ለመውሰድ የሚፈልጉ ባለሃብቶች መኖራቸው ነው ብለዋል።
በግብርና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ብድር እንዲያቀርብ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሃላፊነት ተሰጥቶት እንደነበር ይታወሳል።
ብዛት ያላቸው ባለሃብቶች ይህን ዕድል በመጠቀም ከባንኩ ብድር የወሰዱ ሲሆን ገንዘቡን ግን ለወሰዱበት ሳይሆን ለሌላ ዓላማ እንዳዋሉት በተለያየ ጊዜ ሲነገር ቆይቷል።
ለእርሻ ኢንቨስትመንት ብለው የወሰዱትን ገንዘብ በአራጣ ሲያበድሩት ነበር በሚል ጭምር በአንድ መድረክ ላይ ሲነገር ሠምተናል።
ባለሃብቶቹ የወሰዱትን ብድር ለተባለው አላማ አለማዋላቸው ብቻ ሳይሆን ለባንኩም ባለመመለሳቸው የገንዘብ እጥረት እንዲገጥመው ማድረጉም ተወስቷል።
ልማት ባንክ ዛሬ ላይ በተለይ ዝናብን መሰረት አድርገው ለሚያለሙ ባለሃብቶች ብድር መስጠት እንደከበደው አቶ ደረጄ ተናግረዋል።
የመሰረተ ልማት ችግሮችም ባለሃብቶቹ በሚፈለገው ልክ ወደ ልማት እንዳይገቡ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ስራ አስፈጻሚው ነግረውናል።
ባለሃብቶቹ ከልማት ባንክ የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ ማግኘት ባለመቻላቸው እየገጠማቸው ያለውን ችግር ለመፍታት አማራጭ የብድር ማግኚያ መንገዶች መመቻቸታቸውን አቶ ደረጀ ተናግረዋል።
አስመራቾችን ከባለሃብቶች ጋር በማስተሳሰር እንዲሰሩ እየተደረገ እንደሚገኝም ሠምተናል።
ይኸኛው አሰራር በተለያዩ ክልሎች የተሰማሩ ባለሃብቶች ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳቱን ስራ አስፈጻሚው ነግረውናል።
በራሳቸው ችግር ወደ ስራ ያልገቡ ባለሃብቶችን ፍቃድ ደግሞ ክልሎች እየሰረዙ ነው ሲሉ አቶ ደረጀ ነግረውናል።
ክልሎች የፍቃድ ስረዛ እርምጃውን እየወሰዱ ያሉት መሬቱን ያቀረቡት እነሱ ስለሆኑ ነው ብለዋል።
ንጋቱ ረጋሣ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments