የካቲት 29 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Mar 8
- 2 min read
ፖላንድ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን ስራ ላይ ልታውል ነው፡፡
እድሜያቸው ለአቅመ ውትድርና የደረሰ የአገሪቱ ወንዶች በሙሉ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል መባሉን NBC ፅፏል፡፡
ውጥኑን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ እወቁልን ብለዋል፡፡
የአገሪቱን መደበኛ ወታደሮች ብዛት ወደ 500 ሺህ ለማሳደግ መታሰቡ ተጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ መደበኛ ወታደሮች ብዛት 200 ሺህ ነው፡፡
ሴቶችም እንደ ሁኔታው ለወታደራዊ ስልጠናው ሊጋበዙ እንደሚችሉ ተስክ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪዎች የመጓጓዣ ሔሊኮፕተር ላይ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት 28 የመንግስት ጦር ባልደረቦች ተገደሉ ተባለ፡፡
በመጓጓዣ ሔሌኮፕተሯ ላይ በተፈፀመ ጥቃት 27 ወታደሮች እና በስፍራው የነበረው የደቡብ ሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል መገደላቸውን ሱዳን ፖስት ፅፏል፡፡
አንድ የሰላም አስከባሪም መገደሉ ታውቋል፡፡
ሒሊኮፕተሯ ወደ ስፍራው ያመራችው በታጣቂዎች ከበባ ውስጥ የሰነበቱ የጦር ባልደረቦችን ከዚያ ለማውጣት ነበር፡፡
አወጣጡ ከመከናወኑ አስቀድሞ የተፋላሚዎቹ ፈቃደኝነት የተገኘበት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በአፐር ናይል ናስር በተባለው አካባቢ የሚካሄደው ውጊያ ቀደም ሲል የተደረሰውን አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ስጋት ላይ መጣሉ ይነገራል፡፡
በናስር ጥቃት የከፈቱት የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት ሪያክ ማቻር ደጋፊ ሚሊሺያዎች ናቸው ይባላል፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስትም በዚሁ ጉዳይ ሲቪል እና ወታደራዊ ሹሞችን ማሰሩ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
የደቡብ ሱዳን የብሔራዊ አንድነት መንግስት የእርስ በርስ መተማመን የራቀው እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክይኑን ጦርነት ለማስቆም ከዩክሬይን ይልቅ የሩሲያ መሪዎች ለንግግር እየቀለሉኝ ነው አሉ፡፡
ትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ የዩክሬይኑን ጦርነት በፍጥነት አስቆመዋለሁ ሲሉ መሰንበታቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ባለፈው ሳምንት አርብ ከዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ያደረጉት ንግግር ጭቅጭቅ እና ንትርክ የበዛው ነበር፡፡
የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ከዚህ በኋላ ግንኙነቱን ለማለዘብ እየሞከሩ መሆኑ ይነገራል፡፡
በሌላ በኩል ትራምፕ በሩሲያ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ለመጣል ጉዳዩን እያጤኑት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣሌ አይቀርም ያሉት ሩሲያ ትናንት ከምንግዜው በከፋ ሁኔታ በዩክሬይን የኤሌክትሪክ ማመንጫ እና ማስተላለፊያ አውታሮች ላይ መጠነ ሰፊ ድብደባ መፈፀሟን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
ሩሲያ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ያልተጣለባት ማዕቀብ እንደሌለ ይነገራል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Commenti