‘’የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ህፃናት ለማሰልጠን በልገሳ ከውጪ የገባ ኮምፒውተር በጉምሩክ ተይዞብኝ 6 ዓመት ሆነው’’ ራዕይ የህፃናት መርጃ
- sheger1021fm
- Nov 13, 2025
- 2 min read
ህዳር 4 2018
የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ህፃናት ለማሰልጠን ሊውል የነበረ እና በልገሳ ከውጪ ሀገር የገባ ኮምፒውተር በጉምሩክ ተይዞብኝ 6 ዓመት ሆነው ሲል ራዕይ የህፃናት መርጃ ድርጅት ተናገረ፡፡
ጉምሩክ ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም፡፡
ከ300 በላይ በአዕምሮ እድገት ውስንነት እንዲሁም በኦቲዝምና በሌላም ምክንያት ልዩ ድጋፍ የሚሹ ህፃናትን እየደገፈ እንደሆነ የሚናገረው ድርጅቱ፤ የሚደግፋቸው ልጆች በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ 7 የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአካቶ ትምህርት እየተማሩ ጎን ለጎን የእደጥበብ ሙያንና ሌላውንም ተሰጧቸውን እንዲያዳብሩ ማድረጉን ተናግሯል፡፡
የድርጅቱ መስራችና ዳይሬክተር ፅጌ ጥበቡ(ዶ/ር) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጠርተው ስለ ስራው ባብራሩበት ወቅት ልጆቹ እንዲሰለጥኑበት ለማድረግ 106 ኮምፒውተሮችን ከአሜሪካን ሃገር በልገሳ አሰባስበን ወደ ሃገር ቤት ብናስገባም ላለፉት 6 ዓመታት በጉምሩክ እንደተያዘ ጠቅሰዋል፡፡
ራዕይ የህፃናት መርጃ ድርጅት እየሰራሁ ነው ብሎ ከጠቀሳቸው 7ቱ ትምህርት ቤቶች 2ቱ ማለትም ሲቢስቴ ነጋሲ እና ትንቢተ ኤርሚያስ ቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ት ቤቶች፤የተባለው ኮምፒውተር ይመጣል ብለን ለልጆቹ የኮምፒውተር ላብራቶሪ ክፍል አሰናድተ፤ መምህራንንም አሰልጥነን ብንጠብቅም በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተማሪዎቻችን ወደ ኋላ ቀርተውብናል፤የሚመለከተው አካል ችግሩን ቢፈታልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አትሌት መሰረት ደፋርን የክብር አምባሳደር አድርጎ የሰየመው ድርጅቱ በተለይ በሽመና፣በተሰጥኦ ማበልፀጊያና በሌላውም ለሚያሰለጥናቸው ከ3መቶ በላይ ልጆች ያለው ቦታ በጣም ጠባብና የማያፈናፍን ነው ያሉት ዳይሬክተሯ ዶክተር ፅጌ ሰፋ ያለና ሁሉንም አይነት አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ለመገንባት ውጥን አለን፤ ከመንግስት የቦታ ድጋፍ ቢደረግል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
አትሌት መሰረት ደፋርም በጎ ስሜን ተጠቅሜ የተባሉትን የድርጅቱን ችግሮች ለመቅረፍ እሰራለሁ ስትል ቃል ገብታለች፡፡
የድርጅቱን ስራ ተዘዋውሮ የተመለከተው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በበኩሉ፤ ከተደገፉ ለሃገር ተዓምር የሚሰሩ በድርጅቱ የሚደገፉ ልጆች እንዳሉ ማየቱን ጠቅሶ ለልጆቹ የተቻለውን እንደሚደግፍ ቃል ገብቷል፤ አቶ ፋሲካው ሞላ የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ናቸው፡፡
በማዕከሉና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከሚያሰለጥናቸው ከ3 መቶ በላይ ልጆች ውጭ ወደ ድርጅቱ መቀላቀል የሚፈልጉ በርካታ ተጠባባቂዎች እንዳሉና በቦታ ጥበት ምክንያት መቀበል እንዳልቻሉም ከሃላፊዋ ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments