የነሐሴ 6 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች
- 1 day ago
- 2 min read
በደቡብ አፍሪካ በአንድ የማዕድን ዝቃጭ ማስወገጃ ስፍራ መደርመስ 14 ሰዎች የሞቱበት አደጋ እየተመረመረ ነው ተባለ፡፡
ሌሎች 8 ሰዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡፡
በዝቃጩ ውስጥ የተቀበሩ ሌሎች ሰዎች ሳይኖሩ አይቀሩም ተብሏል፡፡
በአደጋው የሞቱት እና አካላዊ ጉዳት የገጠማቸው ሕገ-ወጥ የማዕድን ሰራተኞች መሆናቸው ታውቋል፡፡
አደጋው የደረሰበት ከተዘጋ የቆየ የማዕድን ስፍራ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
ስፍራው ቀደም ሲል ፕላቲኒየም እና ሌሎችም ማዕድናት ሲመረቱበት የቆየ ነው ተብሏል፡፡
የሊባኖስ ፓርላማ የሞት ቅጣትን የሚያስቀር ህግ አፀደቀ፡፡
የፓርላማው አባላት የሞት ቅጣትን የሚያስቀረውን ህግ ያፀደቁት በአብላጫ ድምፅ እንደሆነ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የሊባኖሱ የፍትህ ሚኒስትር የህጉን መፅደቅ ታሪካዊ ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ህጉ ከመፅደቁም አስቀድሞ በአገሪቱ ላለፉት 22 አመታት አንድም የሞት ቅጣት እንዳልተፈፀመ መረጃው አስታውሷል፡፡
ከእንግዲህ በሊባኖስ እስከ ሞት ቅጣት የሚያደርስ የፍርድ ውሳኔ በእድሜ ይፍታህ እስር ይቀራል ተብሏል።
የእድሜ ይፍታ የእስር ቅጣቱ ከባድ የጉልበት ስራንም እንደሚጨምር ተጠቅሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር የሆርሙዝን የባህር መተላፊያ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል አሉ፡፡
ወደ ኢራን ወደብ በማምራት ላይ የነበረ የፓናማን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ የጭነት መርከብ በ2 ሚሳየሎች መመታቱን ትራምፕ እንደተናገሩ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
የፓናማን ሰንደቅ ዓላማ በሚያውለበልበው የጭነት መርከብ እና በባህረኞቹ ላይ ስለደረሰው ጉዳት በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
ያም ሆኖ ትራምፕ መርከቡን ከጥቅም ውጭ አድርገነዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
መርከቡ የተመታው ወደ ኢራን ወደብ እንዳያመራ የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለማክበሩ እንደሆነ ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
በኢራን በኩል የአገሪቱ የብሔራዊ ደህንነት ምክር የበላይ ሞኸሰን ሬዛይ ኢራን ለአሜሪካ ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ካልተመለሱ የሆርሙዝን ወሽመጥ መዝጋታችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ኢራን ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ፣ የአሜሪካ የባህር ከበባ እንዲቀር ፣ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ተይዞባት የሚገኝ ገንዘብ በሙሉ እንዲለቀቅ መጠየቋን መረጃው አስታውሷል፡፡
በሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ የአሜሪካ እና የኢራን ውዝግብ በመባባሱ በአለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሜል መልሶ ወደ 90 ዶላር ማሻቀቡ ታውቋል፡፡
በቀይ ባህር ባብኤል መንደብ የባህር መተላለፊያ ወሽመጥ ሁቲዎች በሚሳየል ጥቃት አድርሰውበታል የተባለ መርከብ እየጋየ ነው ተባለ፡፡
የመርከቡ 4 ባህረኞች መገደላቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በ10 ሌሎች ባሕረኞች ላይ ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው አለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግስት የባህር ወሰን ጠባቂዎች ተናግረዋል፡፡
የየመን መንግስት የባህር ወሰን ጠባቂዎች የተመታው የንግድ መርከብ ነው ብለዋል፡፡
ሁቲዎቹ በፊናቸው የጦር መሳሪያ ሲያጓጉዝ የነበረን መርከብ በባብኤል መንደብ ወሽመጥ መምታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሁቲዎች እና ሳውዲ አረቢያም በጦር ነገር መፈላለጋቸው እየተባባሰ ነው ይባላል፡፡
ሳውዲ አረቢያ በቅርቡ በቀይ ባህር ፣ በባብኤል መንደብ እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የመርከቦችን ሰላማዊ ምልልስ ለማረጋገጥ የታለመ ነው የተባለው የ14 አገሮች ጥምረት በመሪነት የመሰረችው በቅርቡ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
_edited.jpg)



Comments