top of page

በአዲስ አበባ አጀንዳ ላይ የመከረውን ተመካካሪ ቡድን ጨምሮ ስምንቱም በአምስት መቶ ተሳታፊዎች የተቋቋሙ ቡድኖች በየቡድናቸው ሲመካከሩ ቆይተው በምክረ ሐሳቦች ላይ መስማማታቸውን ኮሚሽኑ ተናገረ።

  • 34 minutes ago
  • 1 min read

ነሐሴ 7 2018


በአዲስ አበባ አጀንዳ ላይ የመከረውን ተመካካሪ ቡድን ጨምሮ ስምንቱም በአምስት መቶ ተሳታፊዎች የተቋቋሙ ቡድኖች በየቡድናቸው ሲመካከሩ ቆይተው በምክረ ሐሳቦች ላይ መስማማታቸውን ኮሚሽኑ ተናገረ።


የምክክር ሂደቱን አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ፣ ሁሉም ተመካካሪ ቡድኖች በቀረቡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ተስማምተው መፈረማቸውን አስረድተዋል።


አከራካሪ ሆኖ የሰነበተው ቡድን 7 ወይም በአዲስ አበባ ላይ የሠራው ቡድን በምክረ ሐሳቡ ላይ መግባባት ላይ ደርሷል ተብሏል።


"በዚህ ሂደት ውስጥ አለመግባባቶች፣ ግጭቶች አልነበሩም አይባልም። በመኖራቸው ምክንያት ግን ይህ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን የበለጠ አረጋግጦልናል። እነዚያ ግጭቶች ተፈተው፣ ተደማምጠው፣ ወደ አንድ የጋራ ሐሳብ፣ አማካይ ሐሳብ ላይ ደርሰው ስምንቱም ቡድኖች ሥራቸውን እያጠናቀቁ ነው" ሲሉ ኮሚሽነሯ አስረድተዋል።


በዚህም እያንዳንዱ ቡድን 15 ሰዎችን መርጦ ምክረ ሐሳቦችን የማመሳከር ሥራ ዛሬ ከሰዓት ጀምሯል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሯ።


"እነዚህ ስምንት የምክክር ቡድኖች ያዘጋጇቸውን እና የተስማሙባቸውን ምክረ ሐሳቦች የሚያጣጥም እና የሚቃረኑ ነገሮች እንዳይኖሩ የሚጠነቀቅ ወይ ደግሞ ድግግሞሾች ያሉባቸውን ምክረ ሐሳቦች ወደ አንድ ለማምጣት የሚሠራ ቡድን ተቋቁሟል። በስምንቱም ቡድን ተመርጠው ጨርሰው ሥራቸውን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይጀምራሉ። እነሱ የሚሠሩት ሥራ አጠቃላይ ለምናቀርበው ምክረ ሐሳቦች አንድ ወጥነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚሠራ ሥራ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።


ከዚህ ባሻገር አንዳንድ ቅሬታ የሚያቀርቡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ቅሬታዎች ኮሚሽኑ ባለው የቅሬታ አፈታት ሥነ ሥርዓት መሠረት ጉዳዩ እየተጠና ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ተናግረዋል።


በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው "ሦስት አራተኛው ሥራችን እየተጠናቀቀ ነው" ሲሉም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።


ያሬድ እንዳሻው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page