የተከለከሉ ፕላስቲኮችን ሲያከፋፍሉ የተገኙ 46 የምርት አከፋፋዮች እንዲዘጉ መደረጉ ተሰማ።
- 9 hours ago
- 2 min read
ሐምሌ 18 2018
የተከለከሉ ፕላስቲኮችን ሲያከፋፍሉ የተገኙ 46 የምርት አከፋፋዮች እንዲዘጉ መደረጉ ተሰማ።
ይህንን የሰማነው የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዛሬ ባስጀመረው 3ኛ ዙር “ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ “ የከተማ አቀፍ መድረክ ላይ ነው።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በፕላስቲክ ብክለት መከላከል ቁጥጥር ስራ 150 ልዩ ልዩ አካላትን ቀጥቼ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ከቅጣት ገቢ መሰብሰቡ ችያለው ሲል ተናግሯል።
በሌላ በኩል በወንዝ ብክለት መከላከል ቁጥጥር ላይ ሰፊ ስራ ሰርቻለሁ ያለው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት አመት ፍሳሻቸውን ወደ ወንዝ በለቀቁ ተቋማት ላይ ከተወሰደ እርምጃ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተነግሯል።
የፍሳሽ ብክለት ያስከትላሉ የተባሉ 12ሺህ ግለሰብ እና ተቋማት ላይ የመለየት ስራ መሰራቱም ተነግሯል።
ከ16ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ተቋማት እና ግለሰቦች የፍሳሽ ማከማቻ (ሴፍቲ ታንከር) የሌላችው እንዲገነቡ፣ ወደ ወንዝ የሚሄዱ መስመሮችን በማቋረጥ ከፍሳሽ መስመሮች ጋር የማገናኘት ስራ ተሰርቷልም ተብሏል።

የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ እሸቱ ለማ (ዶ/ር )ተቋሙ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ ከሚሰራባቸው ዘርፎች አንዱ የአየር ብክለትን መቆጣጠር መሆኑን አንስተው ባለፉት ሁለት አመታት በአየር ብክለት መከላከል ዙሪያ በተሰራ ስራ ከ1.2 ሚሊዮን ቶን በላይ የሙቀት አማቂ ጋዝ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
አደገኛ ቆሻሻ (ኬሚካሎች) በትምህርት ቤቶች ፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና በሌሎችም ተቋማት ተከማችተው ይገኛሉ ያሉት ሀላፊው የአደገኛ ኬሚካል ብክለት መከላከል ላይም ሰፊ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በዚህም ከ 6ሺህ ቶን በላይ በደረቅ መልክ፣ ከ 1ሺህ 800 ሊትር በላይ በፈሳሽ መልክ ፣ ከ420 በላይ በጠርሙስ እንዲሁም ከ 9ሺህ በላይ ደግሞ በፓኬጅ አደገኛ ኬሚካሎች እንዲወገዱ መደረጉንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ባለፉት አምስት አመታት በአዲስ አበባ ከ90 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉ ተነግሯል።
ከተተከሉት መካከል 85 በመቶው መፅደቁንም ሰምተናል።
የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2.8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማደጉን ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዛሬ ያስጀመረው ፕሮግራም በመጪዎቹ 3 ወራት በፕላስቲክ፣ በአደገኛ ቆሻሻና በድምፅ ብክለት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን የሚሰራበት ነው ተብሏል።
የፕሮግራሙ አላማም ዘላቂ የፅዳት ባህልን መገንባት፣ የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤን ማሳደግና ለነዋሪዎች ምቹና ጤናማ አካባቢን መፍጠር ነው ሲባል ሰምተናል።
ፍቅሩ አምባቸው
_edited.jpg)
