የሐምሌ 27 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች
- 1 day ago
- 2 min read
በኢራን ለጠላት ሲሰልሉ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በሞት ተቀጡ፡፡
ሁለቱ ሰዎች በሞት የተቀጡት በፍርድ ቤት የእስራኤል ሰላዮች በመሆን ጥፋተኝነታቸው ስለተረጋገጠባቸው ነው መባሉን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በሞት የተቀጡት ግለሰቦች የወታደራዊ እና የደህንነት ተቋማትን መገኛ አመልካች መረጃዎችን ለእስራኤሉ የውጭ የስለላ ተቋም ሞሳድ ባልደረቦች ሲያቀብሉ ነበር ተብሏል፡፡
የፅሁፍ እና የምስል መረጃዎችን ለሞሳድ እንደላኩ ተረጋግጦባቸዋል ተብሏል፡፡
እስራኤል ኢራን ውስጥ የስለላ እጇ በጣሙን የረዘመ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ኢራን ውስጥ ከዚህ ቀደምም ለእስራኤል ሰለላ ሲያቀላጥፉ ነበር የተባሉ በርካታ ሰዎች በሞት መቀጣታቸው መረጃው አስታውሷል፡፡
በሱዳን ዳርፉር በባህላዊ የፍርድ ስፍራ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት 35 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተናገሩ፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር ስሙ በጥቃት አድራሽነት በክፉ እንደተነሳ ፍራንስ 24 ፅፏል፡፡
በጥቃቱ ከተገደሉት ሌላ የቆሰሉም እንዳሉ ተነግሯል፡፡
ጥቃት የተሰነዘረበት መንደር በRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ይዞታ እጅ የሚገኝ ነው ተብሏል፡፡
ጥቃቱ በሱዳን መንግስት ጦር ተፈፅሟል ቢባልም ጦሩ ግን በዚህ ጉዳይ እንዲህም ነው እንዲያም ነው አላለም፡፡
በሱዳን መንግስት ጦር እና በ RSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል ጦርነት ሲካሄድ ከ3 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡
የጦርነቱ ማስቆሚያ አንዳችም ምልክት አይታይም፡፡
በግሪክ ከተቀሰቀሰ የሰነበተው የሰደድ እሳት የጥፋት አድማሱን እያሰፋ ነው ተባለ፡፡
የሰደድ እሳቱ በ12 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የነበረን ደን ፣ ቁጥቋጦ እና የእርሻ ስፍራ እንዳልነበረ አድርጎ ማውደሙን AFP ፅፏል፡፡
የሰደድ እሳቱን ለመከላከል ተሰልፈው ከነበሩት መካከል የ3 የቃጠሎ ተከላካዮች ህይወት ማለፉ ተሰምቷል።
የሰደድ እሳቱ በተለያዩ ግዛቶች ከስፍራ ስፍራ እየተዛመተ ነው ተብሏል፡፡
ከፍተኛ ነፋስ ከሙቀት ማዕበሉ ጋር ተዳምሮ የሰደድ እሳቱን መዛመት የመግታቱን ጥረት አዳጋች ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡
እንደ ስፔን እና ፈረንሳይ ያሉት አገሮችም በሰደድ እሳት መዛመት ክፉኛ እየተፈተኑ ያሉ አገሮች እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል፡፡
ዘግየት ብሎ በተሰማ መረጃ በግሪክ በሰደድ እሳቱ ማጥፋት ተግባር ላይ የነበሩ ሁለት ሔሊኮፕተሮች በአየር ላይ በመላተማቸው የአንዱ ሒሊኮፕተር 2 ሞተዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካ የኢራኑን ጦርነት በተመለከተ ዲፕሎማሲን እና የጦር ዛቻን እየቀላቀለች ነው ተባለ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የጦርነት ማስቆሚያው ድርድር በዛሬው እለት እንደሚጀመር መናገራቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሔግዚስ ከኢራን ጋር የሚካሄደው ድርድር ከተጨናገፈ አገሪቱን በከባዱ በጦር ለመምታት ተዘጋጅተናል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ሔግዜስ አእንደተናገሩት ድርድሩ ከተጨናገፈ የአሜሪካ ጦር በኢራን ላይ ከ2ኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ድብደባ ለመፈፀም ተሰናድቷል፡፡
የኢራኑ ፕሬዘዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ደግሞ አሜሪካ ሁለቱ አገሮች ቀደም ሰል የፈረሙትን የጦርነት ማስቆሚያ የመግባቢያ ስምምነት ልታከብር ይገባል ብለዋል፡፡
አሜሪካም ሆነች ኢራን በየፊናቸው በስምምነት ጣሽነት እየተካሰሱ ነው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሰላም ድርድሩ በዛሬው እለት ይቀጥላል ቢሉም ድርድሩን በተመለከተ ከኢራን ሹሞች በኩል በቀጥታ የተሰማ አስተያየት የለም፡፡
የኔነህ ከበደ
_edited.jpg)

Comments