top of page

ባለፉት 10 ዓመታት ኤል ኒኖ በኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ተከሰቷል።

  • 1 day ago
  • 2 min read

ሐምሌ 28 2018


ባለፉት 10 ዓመታት ኤል ኒኖ በኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ተከሰቷል።


በ2007/08 እና ከሦስት ዓመታት በፊት በተወሰኑ ቦታዎች ላይ አጋጥሟል።


በእነዚህ ጊዜያት እንስሳት ሞተዋል፤ የግብርና ምርት መጠን አሽቆልቁሏል፤ ገበሬውም ለገበያ እና ለቤቱ የሚያቀርበውን ምርት ለማግኘት መቸገሩን የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ይናገራል።


ታዲያ ዘንድሮ ይከሰታል የተባለው የኤል ኒኖ ክስተት ጉዳት እንዳያደርስ ወይም ጉዳቱን ለመቀነስ የምርምር ተቋማት ምን ሠርተዋል? ከባለፉት ችግሮችስ ምን ያህል ትምህርት ተወስዷል? ጉዳዩን በተመለከተ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትን ጠይቀናል።


በኢንስቲትዩቱ የግብርና ኢኮኖሚ ምርምር ዳይሬክተር ታደለ ማሞ (ዶ/ር) ፤ እስካሁን ድረስ በኤል ኒኖ ከሚደርሰው ጉዳት አንጻር ሲታይ ተገቢውን ትምህርት ወስደን እየተዘጋጀን ነው ማለት አይቻልም ይላሉ።


ዘንድሮ ይከሰታል ለተባለው ችግር በቂ ዝግጅት መደረግ የነበረበት ከሁለት እና ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፤ "እንደ ምርምር ተቋም ላለፉት ሁለት ዓመታት ፈጥነው የሚደርሱ እና ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በምርምር ስናወጣ ነው የሰነበትነው፤ የማሰራጨቱ ሥራ ግን ገና አሁን ነው የተጀመረው" ብለዋል።


ከሦስት ዓመት በፊት በቦረና እና በአካባቢው የተከሰተውን ማስታወስ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፣ አርብቶ አደሩ የነበረውን ሀብት ለማጣት ተገዶ እንደነበር አስረድተዋል።


የኤል ኒኖ መከሰት በኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የሚያነሱት ታደለ ማሞ (ዶ/ር) ፣ ክስተቱ የምርት መቀነስ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡


በዚህም የተነሳ የምግብ ዋጋ ግሽበት ሊከሰት እንደሚችል አስጠነቅቀዋል።


አሁንም ቢሆን የከፋ ችግር እንዳይከሰት ከወዲሁ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲወሰድ ታደለ ማሞ (ዶ/ር) ይመክራሉ።


በምርምር ማዕከላት በፍጥነት የሚደርሱና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎች ስላሉ እነሱን ማሰራጨት ይገባል ያሉ ሲሆን፣ ለእንስሳት የሚሆን መኖም በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።


ክረምቱ የዝናብ መጠኑ ከማነሱም በላይ ቀድሞ ሊወጣ እንደሚችል የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፤ መኖ ለእንስሳቱ ማቅረብ ካልተቻለ ቀድሞ የተወሰኑትን በመሸጥ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ መቀነስ እንደሚገባ ተናግረዋል።


መንግሥት ከወዲሁ የኤል ኒኖ ተጽዕኖ የሚበረታ ከሆነ ግብርናው እንዳይንገዳገድ ድጋፍ የሚያደርግበትን መንገድ ሊያስብበት እንደሚገባም መክረዋል።


እንዲህ ዓይነት ትንበያዎች ሲወጡ ችግሩ ሊከሰት ወራት ሲቀሩት ከመሯሯጥ ይልቅ፣ ከምርምር ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት የሚሰጡ መፍትሔዎችን ወደ ሥራ ማስገባት ይሻላል ብለዋል።


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ...



በረከት አካሉ

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page