በኢትዮጵያ ተላላፊ ባለሆኑ እንደ ልብ ያሉ ሕመሞች ምክንያት የሚመጣ የጤና ችግር ለሀገሪቱ የጤና ሥርዓት ተጨማሪ ሥጋት ሆኗል ተባለ።
- 1 day ago
- 2 min read
ሐምሌ 28 2018
በኢትዮጵያ ተላላፊ ባለሆኑ እንደ ልብ ያሉ ሕመሞች ምክንያት የሚመጣ የጤና ችግር ለሀገሪቱ የጤና ሥርዓት ተጨማሪ ሥጋት ሆኗል ተባለ።
ከልብ ሕመም ጋር በተያያዘ የሚደርስ የጤና ቀውስን ለመቀነስ ሕክምናው እንዲሁም ቅድመ - መከላከሉ ላይ በስፋት መሠራት አለበት ተብሏል።
ከልብ ሕክምና ተደራሽነት፣ የጤና ፖሊሲን ማሻሻል እና ምርምር ላይ የሚሠራው የፓን አፍሪካን የልብ ሕክምና ማኅበር ሰሞኑን በአዲስ አበባ ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ ከልብ ሕመም ጋር የተገናኙ የጤና ችግሮች የአፍሪካ ከፍተኛ የጤና ሥጋት እየሆኑ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአህጉሪቱ ከልብ ሕክምና ጋር በተገናኘ ያሉ ፈተናዎችን በመለየት፣ ሰፊ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እና የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲደረግ ለመንግሥታት ግብዓት የሚያቀብል ውይይት እንደሆነ የነገሩን የኮንፈረንሱ ሊቀመንበር እንዲሁም ከፍተኛ የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ፕሮፌሰር ከበደ ኦሊ ናቸው።
ከልብ ሕመም ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች በቂ የሕክምና አገልግሎት አለመኖር ተጨማሪ ችግር እየሆነ መምጣቱንም ፕሮፌሰር ከበደ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት እና የውስጥ ደዌ እና የልብ ሕክምና ሰብስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ናትናኤል ታዬ በበኩላቸው፣ የልብ ሕመምን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ለሕክምና የሚጠይቁት ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ቀድሞ መከላከሉ ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ጫናው እየጨመረ የመጣውን የልብ እንዲሁም ተያያዥ ሕመሞች ለመከላከልና የሕክምና ሥራውን ለማስፋፋት ምን እየተሠራ ነው? ስንል የጠየቅናቸው በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ስለሺ ጋሮማ፣ ዓለም አቀፍ እንዲሁም በኢትዮጵያ ደረጃ የልብ ሕመም ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ብዙ ችግር ያደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም በሽታውን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ፤ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ፣ በአመጋገብ እና በአካላዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል በፌደራል ደረጃ የወጡ የአፈጻጸም መመሪያዎችን ወደ ክልል በማውረድ በጤና ሚኒስቴር በኩል እየተሠራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ እንደ ካንሰር፣ ልብ፣ ስኳር እና ሌሎች ተላላፊ ባልሆኑ ሕመሞች ምክንያት የሚመጣው የጤና ችግር በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩንና ከሚከሰቱ ሞቶች በእነዚህ ሕመሞች የሚመጣው ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን እንደሚያዝ ተገልጿል።
ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የልብና ደም ሥር በሽታዎች ለብቻቸው ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት ያሳያል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ...
ምህረት ስዩም
_edited.jpg)
