በ2018 በጀት ዓመት ከ1.2 ቢሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
- 1 day ago
- 2 min read
ሐምሌ 23 2018
በ2018 በጀት ዓመት ከ1.2 ቢሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
በየዓመቱ በሀገሪቱ የሚገኘው የምርት መጠን እያደገ እንደሚመጣ ሪፖርቶች ያመልክታሉ።
በገበያው ውስጥ ግን የምርት ዋጋ ከአመት አመት እየጨመረ እንጂ ሲቀንስም አይታይም።
ይህ ለምን ሆነ? እውነትስ ምርቱ ከተመረተ በገበያው ውስጥ ገብቶ ለምን የምርት ዋጋ አይቀንስም? ስንል ባለሙያን ጠይቀናል።
ከተማ በቀለ (ዶ/ር) በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የአግሮ ኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ ናቸው።
በኢትዮጵያ የሚመረተው የግብርና ምርት እየጨመረ ቢመጣም ዋጋ ሊቀንስ ያልቻለው የማምረቻ ወጪ በዚያው ልክ እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነ ከተማ በቀለ (ዶ/ር) ይናገራሉ።
ለምሳሌነትም ከአምስት ዓመት በፊት አንድ ኩንታል ማዳበሪያ በ5,000 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ገበሬው አንድ ኩንታል ማዳበሪያ እሳቸው ባሉበት አካባቢ በ14,000 ብር እየገዛ ይገኛል ሲሉም ያብራራሉ።
«ግብርናው እያደገ ቢሄድም ማደግ ካለበት አንፃርና በሚፈለግበት ደረጃ አይደለም እያደገ ያለው። ምክንያቱ የህዝብ ቁጥሩ የሚጨምርበት መንገድና ግብርናው የሚያድግበት ፍጥነት ባለመጣጣሙ ነው።
የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት እድገት ለወደፊትም በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ የህዝብ ብዛቱና የግብርናው እድገት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲሄዱ ማድረግ አለበት» ብለዋል፡፡
«የማምረቻ ዋጋ መጨመር የግብርና ኢንፍሌሽንን እንዲጨምር ያደርጋል። የማምረቻ ዋጋ ሲጨምር ገበሬውም የሚሸጠው ዋጋ ጨምሮ ነው።
ነጋዴዎች ናቸው ምርቱን ወደ መሃል ከተማ የሚያመጡት እነሱም ዋጋ ጨምረው ነው ለገብያ የሚያቀርቡት። እንግዲህ የኢትዮጵያ መሬት የማዳበርያ ጥገኛ ነው ኬሚካል ማዳበርያ ዋንኛው ግብአት ነው ያ ኬሚካል ማዳበርያ ደግሞ ከውጭ ነው የምናመጣውብለዋል።
ከውጭ ሲመጣ የማረቻ ዋጋ ስለሚንር አንዱ ለምርት መወደድ ምክንያት ይሆናል »ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ገበሬው ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ ለማድረስ አመቺ የንግድ ሰንሰለት እና መሰረተ ልማት አልተዘረጋም ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ምርቱ ያላመረተው ደላላ ዋጋውን በፈለገው መንገድ ያወጣል ያሉት ዶ/ር ከተማ፣ ከገበሬው እስከ ተጠቃሚው ድረስ ያለው የግብይት ሰንሰለት እርዝማኔ ለግብርና ምርት ዋጋ መጨመር ሌላው ምክንያት እንደሆነም ነግረውናል።
በሀገሪቱ ውስጥ የተረጋጋ የግብርና ምርት ግብይት እንዲፈጠር ለማድረግ ከተፈለገ ቅድሚያ ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ሥራም ተጀምሯል፣ መቀጠል አለበት፤ ሌሎችም ለግብርናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ ግብአቶች በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ፖሊሲ መቅረጽ ያስፈልጋል ሲሉም አስረድተዋል።
የገበያ ትስስር፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ እና ገበሬው ራሱ በገበያው ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ማድረግ ከተቻለ በገበያው ላይ የተረጋጋ የግብርና ምርት ዋጋ ማየት ይቻላል ይላሉ።
መንግሥት እንዳፈር ማዳበሪያው ሁሉ ሌሎችም ለግብርና ሥራ የሚያግዙ የኬሚካል ውጤቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ ዕቅድ አውጥቶ ሊበረታ ይገባልም ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም በአንድ ሄክታር የሚገኘውን የምርት መጠን ማሳደግ ላይም በምርምር የታገዙ ሥራዎች መከናወን እንደሚገባቸው ነው የጠቆሙት።
በረከት አካሉ
_edited.jpg)



Comments