top of page

የሐምሌ 22 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

  • 1 day ago
  • 2 min read



አሜሪካ እና ሳውዲ አረቢያ ኢራቅ ውስጥ በአፍቃሪ ኢራን ታጣቂዎች ይዞታ ላይ ድብደባ ፈፀሙ፡፡


ሰሞኑን ሳውዲ አረቢያ በኢራቅ የሚገኙ አፍቃሪ ኢራን ታጣቂዎች በድሮን ጥቃት አድርሰውብኛል ስትል እንደነበር አልጀዚራ አስታውሷል፡፡


ሳውዲ ጥቃቱን ከማውገዝ በተጨማሪ መበቀሌ አይቀርም በሚል ዝታ ነበር፡፡


በኢራቆቹ አፍቃሪ ኢራን ታጣቂዎች ላይ አሜሪካ እና ሳውዲ በፈፀሙት ጥምር ድብደባ ከ20 የማያንሱት መገደላቸው ተሰምቷል፡፡


በሌላ መረጃ አብዮታዊ ዘብ የተሰኘው የኢራን የጦር ክፍል በዮርዳኖስ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር ተቋም ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሰንዝሬያለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የዮርዳኖስ ጦር አምስት ሚሳየሎችን መትቼ አሰናክያለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ስለ ዮርዳኖሱ ጥቃት ከአሜሪካ በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡


የወደፊቱን የሆርሙዝ የባህር መተላለፊያ ወሽመጥ የአካባቢው አገሮች የጋራ አስተዳደር በተመለከተ በኦማን የቀረበው አዲስ ምክረ ሐሳብ ኢራን ተቃውመዋለች ተብሏል፡፡


የሆርሙዝ ወሽመጥ አወዛጋቢነት እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡



በኮንጎ ኪንሻሣ የኢቦላ ሕሙማን ብዛት ከ3 ሺህ 260 በላይ ደረሰ፡፡


በአገሪቱ አዲሱ የኢቦላ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ ከ2 ወር ተኩል በላይ ሆኖታል፡፡


እስካሁንም በወረርሽኙ የ1 ሺህ 437 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጤና መረጃዎች እንደሚያሳዩ ዘ ዋሽንግተን ፖስት ፅፏል፡፡


ኢቱሪ የተሰኘችዋ የምስራቃዊ ኮንጎ ግዛት የወረርሽኙ ተፅዕኖ ያየለባት ነች ተብሏል፡፡


ወረርሽኙ በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት ላይ እንደሚገኝ እለታዊ የጤና መረጃው ያሳያል፡፡


ከ6 አመታት በፊት በአካባቢው ተቀስቅሶ የነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ የከሰመው ከ2 ሺህ 400 በላይ ሰዎችን ከገደለ በኋላ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


ከ10 አመታት በፊት የምዕራብ አፍሪካዎቹን ጊኒን ፣ ሴራሊዮንን እና ላይቤሪያን ያዳረሰው የኢቦላ ወረርሽኝ በታሪክ ተስተካካይ የለውም፡፡


የምዕራብ አፍሪካው የኢቦላ ወረርሽኝ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎችን መጨረሱ ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡



የኢራን ፓርላማ የደህንነት እና የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ አባል የሆኑት ፌዳ ሁሴን ማሌኪ ዩክሬይን በካስፒያን ባህር በንግድ መርከባችን ላይ ለሰነዘረችው የድሮን ጥቃት የእጇን እንሰማታለን ሲሉ ዛቱ፡፡


ቅዳሜ እለት በኢራኗ የንግድ መርከብ ላይ ዩክሬይን በፈፀመችው የድሮን ድብደባ አንድ ባሕረኛ ሲገደል ሌላኛው ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደገጠመው አልጀዚራ አስታውሷል፡፡


ዩክሬይን ጥቃቱን ስለማድረሷ አልሸሸገችም፡፡


የኢራኑ መርከብ ለሩሲያ የሚሰጥ የጦር መሳሪያ የጫነ እንደነበር የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተናግረዋል፡፡


ዩክሬይን ከሩሲያ ጋር የገጠመችው ጦርነት ከ4 አመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡


ምስራቅ አውሮፓዊቱ አገር በካስፒያን ባህር ይህን መሰሉን ጥቃት ስታደርስ የቅዳሜ እለቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡


ዩክሬይን ከቅርብ ወራት ወዲህ በአጥቂ ሰው አልባ በራሪዎች /ድሮኖች/ የራቁ ዒላማዎችን በመምታቱ ረገድ እየተሳካላት ነው ይባላል፡፡



የጃፓንን ደቡባዊ ምዕራብ ክፍል የመታው የመሬት ነውጥ በጥቂቱ 13 ሰዎችን መግደሉን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናይ ታኪአይቺ ተናገሩ፡፡


ነውጡ በርዕደ መሬት መለኪያ /ሬክተር ስኬል/ 7 ነጥብ 1 ሆኖ እንደተመዘገበ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ነውጡ የደረሰው ኩማሞቶ ተብሎ በሚጠራው የአገሪቱ ክፍል ነው፡፡


በአደጋው መሞታቸው ከተረጋገጠው በተጨማሪ በህንፃ ፍርስራሽ ስር የተቀበሩ ብዙዎች እንደሆኑ ተሰግቷል፡፡


በአንድ የገበያ ማዕከል ህንፃ ከነውጡ በተጨማሪ ፍንዳታም አጋጥሟል ተብሏል፡፡


በሌላ የወረቀት ፋብሪካ ደግሞ የጭስ ማውጫ አካል በመደርመሱ ፍርስራሹ የተጫናቸው እንዳሉ ታውቋል፡፡


የአደጋ ተከላካዮች ለነፍስ አድኑ ተግባር እየተረባረቡ ነው ተብሏል፡፡ ያም ሆኖ በስፍራው ያለው እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሙቀት ለነፍስ አድን ሰራተኞቹ ታላቅ ፈተና መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


ነውጡ በርካታ መንገዶችን በመሰባበር ጉዳት አድርሷል፡፡ በኩዩሹ ደሴት በዚሁ የነውጥ አደጋ ምክንያት የባቡር አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ማስገደዱን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ

Recent Posts

See All
የሐምሌ 23 2018 የውጪ ሀገር ወሬዎች

#ግብፅ በግብፅ የሜዴትራኒያን የባህር ዳርቻ የነበረ የአሜሪካ የጋዝ ማጠራቀሚያ መርከብ በድሮን ተመታ ተባለ፡፡ ሁለት የደህንነት ምንጮች መርከቡ በድሮን እንደተመታ አረጋግጠውልኛል ሲል ሬውተርስ ፅፏል፡፡ መርከቡ በድሮን እንደተመታ በእሳት መያያዙ ታውቋል፡፡ ቃጠሎው ወደ ሌላ መርከብም ተጋብቶ ነበር ተብሏል፡፡ ኋላ ግን

 
 
 
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማሳደግ፣አፍሪካዊያን የጋራ መጪ እድላቸውን እንዲቀርፁ ማገዝ ያስፈልጋል ተባለ።

ሐምሌ 23 2018 የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማሳደግ፣አፍሪካዊያን የጋራ መጪ እድላቸውን እንዲቀርፁ ማገዝ ያስፈልጋል ተባለ። የአፍሪካ ሀገሮች እርስ በእርስ፣በአፍሪካና በሩሲያ እንዲሁም አፍሪካ ከተቀረው ዓለም ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሳደግን ዓለማው ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተባበሩት መንግስታት የአ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page