top of page

ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን በጊዜያዊነት መዝጋቷ ተሰማ ።

  • 2 hours ago
  • 1 min read

የካቲት 11/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች



ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን በጊዜያዊነት መዝጋቷ ተሰማ ።


ሰርጡ የተዘጋው *የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ* በአካባቢው የባህር ሃይል ልምምድ ስለሚያደርግ ነው ተብሏል።


ልምምዱ አሜሪካ በአረብ ባህር አካባቢ ወታደራዊ አቅሟን እያደረጀች መምጣቷን ተከትሎ የሚካሄድ እንደሆነ ዘ ቴሌግራፍ ጽፏል።


ዋሽንግተን አውሮፕላን ተሸኳሚ የጦር መርከብን ጨምሮ ወታደሮችን ከዘመን አፈራሽ የውጊያ መሳሪያዎች ጋር ወደ አካባቢው መላኳ ተነግሯል።


የኢራን እርምጃ ሁለቱ ሀገራት አለመግባባታቸውን ለመፍታት በጄኔቫ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ላይ እያሉ የተሰማም ነው።


ኢራን የሆርሙዝ መተላለፊያን ስትዘጋ እንደ ጎርጎርሳውያኑ አቆጣጠር ከ1980ዎቹ ወዲህ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።



ሩሲያ በባልቲክ ሀገራት ላይ ወረራ ከፈጸመች ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት /ኔቶ / ጠንከር ያለ አጸፋ እንደሚገጥማት የኢስቶኒያው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አስጠነቀቁ።


የኔቶ ጥቃት ውስጥ ሩስያ ድረስ የሚዘልቅ እንደሚሆንም ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርጉስ ሣህክና ከ ቴሌግራፍ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።


ሩስያም ይህንን ስለምታወቅ ነገሩን አትሞክረውም ሲሉ መናገራቸው በመረጃው ተጠቅሷል።


ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት የኔቶ እና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ሹሞች ሩስያ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ በባልቲክ ሀገራት ላይ ወረራ ልትፈጽም ትችላለች ማለታቸውን ተከትሎ ነው።


የባልቲክ ሀገራት በመባል የሚታወቁት ኢስቶኒያ ፤ ላቲቪያ እና ሊቱንያ እንደሆኑ መረጃው አስታውሷል።



የፔሩ ፓርላማ የሀገሪቱን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ከስልጣን አነሣ።


ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱ ጆሴ ጄሪ በፓርላማው ከስልጣን እንዲነሱ ድምጽ የተሰጠባቸው በሙስና ወንጀል ተጠረጥረው ነው።


ፕሬዝዳንቱ ከሁለት የቻይና ዜጎች ጋር ያልተገባ ግንኙነት ፈጠረዋል በሚል ምርመራ እንደተጀመረባቸው france 24 ጽፏል።


ዝርዝር ጉዳዩ ግን ይፋ እንዳልሆነ ነው መረጃው የጠቀሰው።


ሁኔታው በፔሩ ያለውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዳያባብሰው ተሰግቷል።


ሀገሪቱ ሚያዝያ ወር ላይ ፕሬዝደንቷን እና የፓርላማ አባላትን ምርጫ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዛለች።


ንጋቱ ረጋሳ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


YouTube : https://shorturl.at/18TS1

WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx

X :- https://x.com/shegerfm?s=2

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page