በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፌስቱላ !
- sheger1021fm
- 6 minutes ago
- 2 min read
በወሊድ ወቅት በተገቢው ሰዓት አስፈላጊውን ህክምና አለማግኘት ብዙ ችግር ያስከትላል፡፡
እንደ መንገድ፣ ገንዘብ፣ የባህል ተጽዕኖ እና በተዛቡ የአመለካከት ችግሮች ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት ባለመሄድ አሊያም ወደ ጤና ተቋማት ከሄዱ በኋላ ተገቢውን ህክምና አለማግኘት ፣ ጥራት በጎደለው ህክምና ፣ የአቅርቦት እጥረት ፣ ተፈላጊው ክህሎት ያለው ባለሙያ ባለመኖር እና ሙያው በሚጠይቀው ሙያዊ የሥነምግባር ጉድለት ምክንያት ሽንት መቆጣጠር አለመቻል ወይም ፌስቱላ ሊከሰት ይችላል፡፡
በወሊድ ወቅት የሚከሰት ፌስቱላ ቁርጠኝነቱ ካለ እና ከህክምና ባለሙያዎች ጋር የተቀናጀ ጥረት ከተደረገ ሙሉ በሙሉ መከላከል እንደሚቻል ባለሙያዎች የሚያምኑ ቢሆንም አንዴ ከተፈጠረ በኋላ ግን አስቸጋሪ አንዳንዴም የማይቻል ነው ይላሉ።
ምክንያቱም ለፌስቱላ የሚያደርሰው ከባድ በሆነው ምጥ ምክንያት የሚዛባው የሰውነት ክፍል ስለሚጎዳ ለህክምና አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡
እንዲሁም ህክምናው ተሳክቶ እንኳን ቀዳዳውን መዝጋት ቢቻል ሂደቱ ከፌስቱላ ባሻገር ከተለያዩ ተዛማጅ ጉዳቶች በተጨማሪ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ስለሚያስከትል የተፈጠረውን የአካል ቀዳዳ መዝጋት ብቻ ሳይሆን የህይወት ቀዳዳዎችን ደግሞ መድፈን ቀርቶ ማጥበብ ላይቻል እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ታዲያ ፌስቱላን ለመከላከል ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
ነፍሰጡር ሴቶች የጤና ክትትል እንዲያደርጉና የጤና ተቋማትን ማስፋፋት እና ይህንን የፌስቱላ ችግር ቀዳሚ አጀንዳችን ብናደርግ የተሻለ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል የሚሉት ባለሙያዎቹ ፌስቱላ መከሰቱ በራሱ እንደ ሰብአዊ መብት ጥሰት ስለሚቆጠር ፌስቱላን መገለጫችን እንዳይሆን መስራት አለብን ይላሉ።
ከባድ ምጥን ተከትሎ ከሚመጣው ሽንት ከመቆጣጠር ችግር ባሻገር በሌሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች አንዲት ሴት ሽንቷን በምትፈልገው መጠን መያዝ ላትችል ትችላለች።
ከወሊድ ውጪ ፌስቱላ በእድሜ መግፋት ፣ በተደጋጋሚ በመውለድ ፣ በስኳር እና በነርቭ ህመም በመሳሰሉት እና አንዳንድ መድሃኒቶችን በመውሰድ ሊከሰት ይችላል። በእዚህ የሚከሰተው የሽንት መቆጣጠር ችግር እንደ ፌስቱላ በማንኛውም ጊዜ የሚከሰት የሽንት ማምለጥ ሳይሆን በማሳል፣ በመሳቅ ፣ በማስነጠስ ፣ ከባባድ እቃዎችን በማንሳት ጊዜ ማምለጥ አንዳንዴም ደግሞ ሽንት መጥቶ ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ ባሰቡ ጊዜ ሳይደርሱ ማምለጥ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ሁለቱም ክስተቶች ታማሚዎችን በብዙ መንገድ ይጎዳሉ። ምንም እንኳን ለሞት ባያደርስም በሚያሳድረው የማህበራዊ ግንኙነቶች ተጽዕኖ ምክንያት ምቾት ይነሳሉ።
መፍትሔው ምንድነው?
በግልጽ በመነጋገር እንደ ባህል ባልዳበረበት ማህበረሰብ ውስጥ የፌስቱላ ችግሮች ሲከሰቱ ህመምተኞቹ ብቻቸውን ስለሚጋፈጡት ይበልጥ ተጎጂ ይሆናሉ። እንዲሁም መፍትሄ እንደሌለው ስለሚያስቡ አሊያም መፍትሄው ቀዶ ህክምና ብቻ እንደሆነ የሚረዱ እንዳሉ ይነገራል።
ነገር ግን እንዲህ አይነት ችግሮች መከላከያም ማከሚያም ዘዴ ያላቸው ሲሆን ከቀዶ ህክምና በፊት ሊተገበሩ የሚችሉ እና ውጤታማ የሆኑ የአኗኗር ዘይቤዎችን መከተል የመስሉ አማራጮች ስላሉ ምልክቶቹ ሲታዩ ለብቻ ከመያዝና ከመጨነቅ ይልቅ ባለሙያን ማማከር እንደሚገባ ተጠቁሟል።
ጤናዎን ይጠብቁ!
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








