top of page

በርካታ ወርቅ አምራች ድርጅቶች አፈፃፀማቸው "እጅግ በጣም ዝቅተኛ" እንደሆነ ተነገረ

  • sheger1021fm
  • 13 minutes ago
  • 2 min read

ህዳር 9 2018


በርካታ ወርቅ አምራች ድርጅቶች አፈፃፀማቸው "እጅግ በጣም ዝቅተኛ" እንደሆነ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ተነገረ።


ይህ የተነገረው በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የማዕድን ሚኒስቴርን የ3 ወራት የስራ ክንውን ሪፖርት ትናንት ህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ባደመጠበት ወቅት ነው።

ree

የወርቅ ልማትን በተመለከተ ወደ ስራ የገቡ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች፤ ለምሳሌ ዋይ ኤም ጂ (YMG) 10.74 ኪሎ ግራም አቅዶ 0.45 ኪሎ ግራም፣ ኢዛና 84.3 ኪሎ ግራም አቅዶ 42.1 ኪሎ ግራም፣ ዙምባራ 19.17 ኪሎ ግራም አቅዶ 3.4 ኪሎ ግራም፣ እስቴላ ትሬዲንግ ኢንዱስትሪ 9 ኪሎ ግራም አቅዶ 5.4 ኪሎ ግራም እንዲሁም ሲዳማ 3 ኪሎ ግራም ለማግኘት አቅዶ ምንም አለማግኘቱ በፓርላማ ጥያቄ አስነስቷል ።


ይህን ተከትሎም የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፍተኛ እና አነስተኛ #የወርቅ_አምራች ኩባንያዎች ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ድርሻቸው ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁሞ ይሁንና ወደ ስራ የገቡ የበርካታ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች አፈፃፀም "እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው" ብሏል።


ኩባንያዎቹ ለምን የእቅዳቸውን ያህል መፈፀም እንዳልቻሉ ቋሚ ኮሚቴው የማዕድን ሚኒስቴርን ጠይቋል።

ree

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) እነዚህ ወደ ስራ የገቡት አምራቾች የየራሳቸው ችግር ያለባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል።


ለምሳሌ ኢዛና የተባለው አምራች ከዚህ በፊት ችግር የነበረበት እንደነበር ጠቅሰው አሁን ጥገና ተደርጎለት ለማምረት "እየሞከረ" ነው ተብለዋል፡፡ኩባንያው የሃይል ጨምሮ በርካታ ሲሉ የገለጹት እና ያልዘረዘሩት ችግር እንደነበረበት ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።


የዋይ ኤም ጂን (YMG) በተመለከተ ደግሞ ኩባንያው አስቀድሞ ስራ ሲጀምር ባህላዊ ወርቅ አውጪዎችን ለማጣራት ስራ መጀመሩን የተናገሩት የማዕድን ሚኒስትሩ ይህም ሃሳቡ መልካም እንደነበር አስረድተዋል። ይህም በምርት ሂደት በከፍተኛ ሁኔታ የሚባክነውን ወርቅ እንደሚያስቀር ጠቁመዋል።


በቀጣይ የኩባንያው ስራ ውጤታማ እንዲሆን ከባህላዊ ወርቅ አውጪዎች ጋር የማስተሳሰር ስራ እንደሚሰራ ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ተናግረዋል። ሁሉም የየራሳቸው ችግር አለባቸው የሚል ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ በርካታ ወርቅ አምራች ድርጅቶች በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገቡ ጠቅሰዋል።


የማዕድን ሚኒስቴርን የሩብ ዓመት ሪፖርት ያቀረቡት ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ባለፉት ሶስት ወራት ከኩባንያዎች 0.86 ቶን ወርቅ ለማግኘት ታስቦ 0.74 ቶን ወርቅ ተገኝቷል ሲሉ አስረድተዋል።

ree

በተመሳሳይ ከባህላዊ ወርቅ አውጪዎች 7.5 ቶን ለማግኘት ታቅዶ 10.46 ወይም የእቅዱን 139 በመቶ ማግኘት እንደተቻለ ሚኒስትር ሃብታሙ ተናግረዋል።


በአጠቃላይ ባለፉት 3 ወራት 12 ቶን ወርቅ ወደ ውጭ ተልኮ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ተብሏል።


እንደራሴዎች ሌላው የማዕድን ሚኒስቴርን የጠየቁት ጥያቄ ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች የማዕድን ምርቶችን ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን ማምጣት አይቻልም። በየብስ ትራንስፖርት ሲያመጡ ደግሞ ቀረጥ በየአካባቢው ይጠየቃሉ ከፊሎቹ ደግሞ ይወረሳሉ ይህ ለምን ሆነ? የሚል ነው።


በተለይ የኦፓል ምርትን ከአማራ ክልል ከወሎ አካባቢ አምራቾች በአውሮፕላን ስለማይፈቀድላቸው በየብስ ትራንስፖርት ይጠቀማሉ። ይህም ደግሞ ለህገ-ወጥ ንግድ በር ከመክፈቱም በላይ ንብረታቸው እንዲወረስባቸው ማድረጉን የምክር ቤት አባላት አምራቾችን በመጥቀስ ተናግረዋል ።

ree

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት በሚኒስቴሩ የማዕድን ግብይት መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ኢዮብ በቀለ (ዶ/ር) ናቸው። በአውሮፕላን እንዳናጓጉዝ ተከልክለናል በሚል የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ "የሲቪል አቬዬሽን ደህንነት መምሪያ የማዕድናትን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የወሰደው የተናጥል ውሳኔ መሆኑን" መሪ ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።


አሁን ይህን ችግር ለመቅረፍ በኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት ማዕድኑን ወደ ውጭ ለመላክ ደብዳቤ ካስገቡ በኋላ ማዕድኑ የተገዛበት ክልል እውቅና ካለው እና ህጋዊ መሆኑ ሲረጋገጥ በአውሮፕላን መላክ ይቻላል። ከዚያ ውጭ ያሉ ቅሬታዎች ግን ህጋዊውን የማይፈልጉ አካላት ናቸው ብለዋል ኢዮብ በቀለ (ዶ/ር)።


ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆኑ አምራቾችን ምክንያታቸው በአግባቡ ተለይቶ በአሰራር እንዲደገፉ አሳስቧል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page