ሰኔ 20 2017 - የውጪ ሀገር ወሬዎች
- sheger1021fm
- Jun 27
- 2 min read
የኢራኑ የበላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ሐሚኒ አሜሪካ ዳግም ጥቃት ካደረሰችብን በቀጠናው የሚገኙ የጦር ሰፈሮቿን እንመታለን አሉ፡፡
የኢራኑ የበላይ መሪ በመንግስታዊው መገናኛ ብዙሃን በተላለፈ መልዕክታቸው በቀጠናው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በሙሉ በዒላማችን ውስጥ ናቸው ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡
ቀደም ሲል አሜሪካ በእስራኤል ተደራቢነት በኢራን የኒኩሊየር ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ድብደባ ፈፅማለች፡፡
ኢራንም በምላሹ በካታር ወደሚገኘው የአሜሪካ የአል ኡዴይድ የጦር ሰፈር የሚሳየል ጥቃት ሰንዝራለች፡፡

የአሜሪካ ሀይሎች በጊዜው ኢራን የተኮሰቻቸውን ሚሳየሎች በሙሉ በአየር መከላከያዎች አክሽፈንባታል ብለዋል፡፡
ኢራን ግን ብድሬን መልሻለሁ እያለች ነው፡፡
ዳግም በአሜሪካ ጥቃት የሚሰነዘርብን ከሆነ ዋሽንግተን ትልቅ ዋጋ ትከፍላለች ብለዋል ሐሚኒ፡፡
የኬንያው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮሜን አገሪቱን ከትናንት በስቲያ ሲንጣት የዋለው ከባድ ተቃውሞ ያልተሳካ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ነበር አሉ፡፡
በእለቱ መዲናዋ ናይሮቢን ጨምሮ በተለያዩ የኬኒያ ከተሞች ታላላቅ ፀረ መንግስት የተቃውሞ ሰልፎች መደረጋቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰልፈኞቹን በተቃዋሚነት የተጋረዱ አሸባሪዎች ናቸው ሲሉ ጠርተዋቸዋል፡፡
ኪፕቹምባ የአገሪቱ የፀጥታ ሀይሎች በሆደ ሰፊነት በወሰዱት የተመጠነ እርምጃ ሥርዓተ አልበኞች ሲሉ የጠሯቸውን ወገኖች የመንግስት ግልበጣ ሙከራ አክሽፈዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የከትናንት በስቲያው የተቃውሞ ሰልፍ በግጭት ጭምር የታጀበ ነበር፡፡
በግጭቱ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ታውቋል፡፡
300 የፖሊስ ባልደረቦችን ጨምሮ ከ400 በላይ ሰዎች የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡
በኬንያ ከቅርብ አመታት ወዲህ የሚደረግ የተቃውሞ ሰልፍ ለሰዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነ ግጭት አስከታይነቱ መደጋገሙ ይነገራል፡፡
በሱዳን RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የሰላም ንግግር ለማድረግ ፈቃደኛም ፤ ዝግጁም ነኝ አለ፡፡
ታጣቂ ሀይሉ ለሰላም ንግግር ፈቃደኛ መሆኑን የተናገሩት የፈጥኖ ደራሹ ሀይል የበላይ አዛዥ የሌተና ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ልዩ አማካሪ ኢዘዲን አል ሳፊ እንደሆኑ አሽራቅ አል አውሳት ፅፏል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር እና የ RSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ ከ2 አመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡
አል ሳፊ ንግግሩ ግልፅ እና በቀናነት ላይ የተመሰረተ ከሆነ ስለ ሰላም ለመደራደር ዝግጁ ነን ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
RSF ለሰላም ንግግር ዝግጁም ፈቃደኛም ነኝ ማለቱ የተሰማው አለም አቀፍ ወገኖች በሱዳን የተኩስ አቁም እንዲደረግ አዲስ ጥረት በጀመሩበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
ይሄን ጉዳይ በተመለከተ የሱዳን መንግስት አቋም ምን እንደሆነ በመረጃው አልተጠቀሰም፡፡
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፖብሊክ በተማሪዎች ተገፋፍቶ መረጋገጥ የ29ኙ ሕይወት ማለፉ ተሰማ፡፡
በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ከፍተኛ ፍንዳታ መድረሱ ተማሪዎቹን በማሸበር ለተገፋፍቶ መረጋገጣቸው ምክንያት መሆኑን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በፍንዳታው ወቅት በትምህርት ቤቱ 6 ሺህ ያህል ተማሪዎች በ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ላይ ነበሩ ተብሏል፡፡
በፍንዳታው እና በጭሱ የተረበሹ ተማሪዎች ራሳቸው ከአደጋ ለማትረፍ እየተሯሯጡ ለመሸሽ ሲሞክሩ መረጋገጡ እንዳጋጠመ ተጠቅሷል፡፡
መጥፎው አጋጣሚ ተፈጠረው የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር በመፈንዳቱ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
በአደጋው ምክንያት የፈተናው ጊዜ ተራዝሟል ተብሏል፡፡
በአገሪቱ በአደጋው ምክንያት የ3 ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ታውጇል፡፡
በተገፋፍቶ መረጋገጡ ሕይወታቸው ካለፈው ሌላ ከ280 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ታውቋል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il












Comments