top of page

ሰኔ 10 2017 – የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 7 hours ago
  • 2 min read

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የካናዳ የቡድን 7 አባል አገሮች ስብሰባ ቆይታቸው አሳጥረው ወደአገራቸው የተመለሱት በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለማስቻል ነው መባሉን አስተባበሉ፡፡


ቀደም ሲል የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአሜሪካው ፕሬዘዳንት የካናዳውን ስብሰባ አቋርጠው የተመለሱት ለተኩስ አቁሙ ጉዳይ ነው ብለው እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


የትራምፕ አስተያየት የተሰማው የእስራኤል እና የኢራን ግጭት ለ5ኛ ቀን ተባብሶ በቀጠለበት አጋጣሚ ነው፡፡

የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ ከ3 የአውሮፓ አገሮች ሹሞች ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር አገሮቹ የእስራኤልን ድብደባ እንዲያወግዙ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡


እስራኤል በኢራን ያልተቋረጠ ድብደባ እየፈፀመች ነው፡፡


ኢራንም ወደ እስራኤል 30 ሚሳየሎችን እንደተኮሰች የጦር ሹሞቿ ተናግረዋል፡፡


ያም ሆኖ አብዛኞቹን ሚሳየሎች አምክነናቸዋል ብለዋል፡፡


ይሁንና ከሚሳየል መከላከያ ጋሻ ያመለጡት በደፈናው ጉዳት ማድረሳቸውን አልሸሸጉም፡፡


በኢራን የቴሕራን ከተማ ነዋሪዎች በብዛት ከተማዋን ለቀው እየወጡ ነው ተብሏል፡፡



በእስራኤል የሚገኙ ሁሉም ቻይናውን አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ታዘዙ፡፡


ምክር እና ትዕዛዙን የሰጠው የቻይና ኤምባሲ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ኤምባሲው ዜጎቹ በተቻለ ፍጥነት በየብስ የድንበር ኬላዎች በኩል ቢወጡ የተሻለ እንደሚሆን መክሯቸዋል ተብሏል፡፡


በተለይም የዮርዳኖስ አቅጣጫ የተሻለው እንደሆነ መክሯቸዋል፡፡


የቻይና ኤምባሲ ዜጎቿ እስራኤልን ለቅቀው እንዲወጡ ያስጠነቀቃቸው የፀጥታው መደፍረስ እየተባባሰ በመምጣቱ ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡


ያም ሆኖ የእስራኤል ጦር አሁን ሁሉም እስራኤላዊያን ከአደጋ መጠበቂያ ስፍራዎች መውጣት ይችላሉ የሚል መልዕክት ማስተላለፉ ተሰምቷል፡፡


በየጊዜው ግን የደህንነት ማስጠንቀቂያዎችን በአንክሮ ሊከታተሉ ይገባል ብሏል፡፡


በሌላ መረጃ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የኢራኑን መሪ አያቶላ ዓሊን ሐሚኒን መግደል ግጭቱን በማባባስ ፋንታ በአጭሩ ይቋጨዋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ግብፅን ጨምሮ 21 የሙስሊም አገራት እስራኤል በኢራን ላይ የምትፈፅመው የጦር ጥቃት አውግዘዋል ተብሏል፡፡



የሩሲያ እና የአሜሪካ የግንኙነት ማሻሻያ ቀጣይ ዙር ንግግር ተሰረዘ፡፡


ቀጣዩ ዙር ንግግር የተሰረዘው በአሜሪካውያኑ ተደራዳሪዎች ጥያቄ መሆኑን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይዋ ማሪያ ዛኻሮቫ መናገራቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ከሆኑ በኋላ ከሩሲያ ጋር ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት የማሻሻል ፍላጎት ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡


በተለይም የዩክሬይኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ድፍርስርሱ ወጥቷል፡፡


ቀደም ሲል በአሜሪካ የሩሲያው አምባሳደር የሁለቱ አገሮች 3ኛ ዙር የግንኙነት ማሻሻያ ንግግር በቅርቡ በሞስኮ ይደረጋል ብለው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ንግግር የተቋረጠበት ምክንያት በዝርዝር አልተጠቀሰም፡፡



የዩጋንዳው ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በአገር ክህደት የሚከሰሱ ዜጎች ጉዳይ በጦር ፍርድ ቤት እንዲታይ የሚፈቅደውን ህግ በፊርማቸው አፀደቁት፡፡


ቀደም ሲል ይሄን መሰሉ ህግ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው ተብሎ እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


በፕሬዘዳንቱ ተፈርሞ ስራ ላይ ይዋል የተባለው ህግ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ ቁሳቁሶች የሚገኙባቸውን ሲቪሎች የተመለከተ ነው ተብሏል፡፡


የህጉ ነቃፊዎች መንግስት ህጉን ስራ ላይ የሚያውለው የተቃዋሚዎቹን አፍ ለማዘጋት አልሞ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ተቃዋሚ እንደራሴዎች ህጉ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሚጋፋ ነው በሚል በሚፀድቅበት ወቅት ራሳቸውን ከተሳትፎ ማግለላቸው መረጃው አስታውሷል፡፡


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page