top of page

ሜታ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሆኑ የአውስትራሊያ አዳጊ ወጣቶችን ገፆቹን እንዳይጠቀሙ አደረጋቸው፡፡

  • sheger1021fm
  • 33 minutes ago
  • 2 min read

ጥር 5/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች



የእነ ፌስ ቡክ እና ኢኒስታግራም የማህበራዊ ድረ ገፆች እናት ኩባንያ (ሜታ) ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሆኑ የአውስትራሊያ አዳጊ ወጣቶችን ገፆቹን እንዳይጠቀሙ አደረጋቸው፡፡


ክልከላው በአውስትራሊያ ስራ ላይ የዋለውን ህግ መሰረት ያደረገ መሆኑን ABC ፅፏል፡፡


አዲሱ የአውስትራሊያ ህግ እድሜያቸው ከ16 አመታት በታች የሆነ አዳጊ ወጣቶች በጭራሸ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን እንዳይገለገሉ የሚከለክል ነው፡፡


አዳጊ ወጣቶች ክልከላውን ተላልፈው የማህበራዊ ትስስር ገፆቹን ሲገለገሉ ከተገኙ አገልግሎት አቅራቢያ ኩባንያዎች የገንዘብ ቅጣት እንዲቆነደዱ ያደርጋል፡፡


አዳጊ ወጣቶችን የማህበራዊ ትስስር ገፆችን እንዳይገለገሉ በማድረግ አውስትራሊያ ቀዳሚዋ አገር ሆናለች፡፡



የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጋር የነበረኝን ሁሉንም የትብብር ስምምነት ሰርዣለሁ አለ፡፡


ውሳኔው የተላለፈው በአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካይነት እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡


ስምምነቶቹ የበርካታ የወደብ ልማቶችን አንዲሁም የደህንነት እና የመከላከያ ጉዳዮችን የተመለከቱ ነበሩ ተብሏል፡፡


የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግስት ከኢሚሬትስ ጋር ተደርሰው የነበሩ ስምምነቶች ከእንግዲህ አያሹኝም ያለው የባሕረ ሰላጤዋ አገር ሉአላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን ተጋፍታለች በሚል ምልክንያት ነው፡፡


በደቡባዊ የየመን ክፍል የመገንጠል ዓላማ አራማጅ ነው የሚባለው የSTC መሪ አይድሩስ አል ዙቤይዲ በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እርዳታ በአየር ወደ አቡዳቢ የኮበለሉት በሶማሌላንድ በኩል እንደነበር ሲነገር ሰንብቷል፡፡


ሶማሊያ ደግሞ በዚህ ድርጊት ሉአላዊነቴ ተጥሷል እያለች ነው፡፡



የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አሜሪካ በፀጥታ ስጋት ግሪንላንድን ወርራ ከምትይዘው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በዚያ የመከላከያ ሀላፊነት ቢሰጠው ይሻላል የሚል አማራጭ አቀረቡ፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደሴቲቱን የአሜሪካ አካል ለማድረግ በሩሲያ ወይም በቻይና ልትወረር ትችላለች የሚል ሰበብ እያቀረቡ ነው፡፡

ትራምፕ ግሪንላንድ ከዴንማርክ በላይ ለደህንነታችን በጣሙን አስፈላጊያችን ነች ማለቱን እንደደጋገሙት አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


የትራምፕ አዝማሚያ በዴንማርክም ሆነ በግሪንላንዳውያን ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡


የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ዛቻ እያወገዙት ነው፡፡


በአርክቲክ ክበብ የምትገኘው የአለማችን ትልቋ ደሴት ግሪንላንድ የዴንማርክ የራስ ገዝ ግዛት ነች፡፡


ግሪንላንድ ከወታደራዊ ፋይዳዋ ባልተናነሰ የውድ ማዕድናት መገኛ እንደሆነችም ይነገራል፡፡



የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተቃውሞ ከምትናጠው ኢራን ጋር በሚነግዱት አገሮች ላይ ተጨማሪ የ25 በመቶ የቀረጥ ታሪፍ እጥልባቸዋለሁ አሉ፡፡


ትራምፕ ከኢራን ጋር ትልቅም ሆነ ትንሽ ንግድ በሚያከናውኑት አገሮች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ በትሩዝ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት እወቁልኝ ማለታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡


እንደ ሩሲያ ፣ ቻይና ፣ ብራዚል እና ቱርክ ያሉ አገሮች ከኢራን ጋር የንግድ ትስስር ያላቸው አገሮች ናቸው፡፡


ኢራቅ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስም ከኢራን ጋር ጥብቅ የንግድ ትስስር ያላቸው አገሮች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡


በከፍተኛ የኑሮ ውድነት መነሻ በኢራን ከተቀሰቀሰ የሰነበተው ሕዝባዊ ተቃውሞ በግጭት ታጅቦ የሰዎች ሕይወት እየነጠቀ ነው ተብሏል፡፡


ትራምፕ በኢራን ጦር ላይ ካሰቡት ወታደራዊ እርምጃ በተጓዳኝ የአገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሽመድመር ቆርጠው መነሳታቸው ተሰምቷል፡፡


ትራምፕ የቀረጥ ታሪፍን ከምጣኔ ሐብታዊ ምክንያቶችም ውጭ ፣ በፖለቲካ መሳሪያትም መጠቀማቸው የተለመደ እዠየሆነ መምጣን መረጃው አስታውሷል፡፡


ዝርዝሩ ባይብራራም አዲሱ የቀረጥ ታሪፍ እርምጃቸው ሳይውል ሳያድር ስራ ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡


የኔነህ ከበደ

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page