top of page

ሚያዝያ  9፣2016 - በኢትዮጵያ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ 3.24 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

በኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው በ10 ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ 3.24 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ፡፡

 

በመጪዎቹ 5 ወራት የነፍስ አድን እርዳታ ለማቅረብ እና ምግብ ነክ ድጋፍም ለማድረግ 1 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተናግሯል፡፡

 

የኢትዮጵያ አለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ከዚሁ አላማ ጋር በተገናኘ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ትናንት ፈንድ ማሰባሰቢ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

 


በዚህም በመጭዎቹ 5 ወራት ያስፈልጋል ከተባለው 1 ቢሊየን ዶላር መካከል 630 ሚሊየን ዶላር ቃል መገባቱን በስብሰባው ላይ የተሳተፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡

 

ይህም ከሚያስፈልገው የተገኘው 5 በመቶ ብቻ መሆኑን ያሳያል ብሏል የተባበሩት መንግስት ድርጅት በድረ ገፁ ባወጣው መረጃ፡፡

 

የገቢ ማሰባሰቢ ፕሮግራሙን የኢትዮጵያና የእንግሊዝ መንግስት በጋራ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመተባበር የተካሄደ ነው ተብሏል፡፡

 

በድርቅ፣ በጎርፍና በግጭት ምክንያት የምግብ እጥረት አጋጥሟቸው እርዳታ የሚያስልጋቸው ሰዎች ቁጥር እስከመጪው መስከረም ወር ወደ 10.8 ሚሊየን ከፍ ሊል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡

 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ መሰረት 4.5 ሚሊየን ተፈናቃዮች የጤናም ጭምር እገዛ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል፡፡

 

በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በሌሎችም ክልሎች ያጋጠመው የምግብ እጥረት ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

 


የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ ብሔራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፍ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም እየሰራ ነው ያለው ሪፖርቱ መንግስት 250 ሚሊየን ዶላር ለመጭዎቹ ወራት መድቦ እየሰራ ነው ብሏል፡፡

 

የተባበሩት መንግስታት አጋች ደግሞ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ ለማገዝና እርዳታ የሚቀርብላቸው ሰዎች ቁጥርም ከፍ አድርጎ ለማዳረስ እየሰራ ነው ሲል በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

 

ትዕግስት ዘሪሁን

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

Telegram:  @ShegerFMRadio102_1

 

 

 

bottom of page