top of page

ሚያዝያ  19፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች


በኬንያ ከባድ ጎርፍ አስከታዩ ዝናብ እንደሚቀጥል ማስጠንቀቂያ ተሰጠ፡፡


በአገሪቱ የሰሞኑ ጎርፍ የገደላቸው ብዛት ወደ 70 ከፍ ማለቱን TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡


ርዕሰ ከተማ ናይሮቢ ሳይቀር የከባድ ጎርፍ ተጎጂ ሆና መሰንበቷ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገሮችም በጎርፉ እየተፈተኑ ነው፡፡


ከባድ ጎርፍ አስከታዩ ዶፍ ዝናብ ኤልኒኖ የተሰኘው የአየር ለውጥ ክስተት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡


በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው ጎርፍ በመሬት መናድ እና መንሸራተትም የታገዘ ነው ተብሏል፡፡




የአሜሪካ መንግስት ለዩክሬይን በአፋጣኝ ፔትሪዮት የሚሳየል መከላከያዎችን አስታጥቃታለሁ አለች፡፡


ከሚሳየል መከላከያዎቹ በተጨማሪ የመድፍ ተተኳሾችንም አቀርብላታለሁ ማለቷን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ለዩክሬይን የሚቀርቡት የሚሳየል መከላከያዎች እና የመድፍ ተተኳሾች የ6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ተብሏል፡፡


አሜሪካ ለዩክሬይን የጦር ድጋፉን የምታቀርበው የሩሲያ የሚሳየል እና የድሮን ጥቃት በበረታባት ወቅት ነው፡፡


በቅርቡ የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች እና የህግ መወሰኛ ምክር ቤቶች ለዩክሬይን የጦር መደገፊያ 61 ቢሊዮን ዶላር ማፅደቃቸው ይታወቃል፡፡


ዩክሬይን ከሩሲያ ጋር በምታካሂደው ውጊያ አብዛኛውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ የምታገኘው ከምዕራባዊያኑ እና ከአጋሮቻቸው ነው፡፡



የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዩክሬይኑ ጦርነት ቻይና ለሩሲያ የምታደርገውን ድጋፍ ልታቆም ይገባል አሉ፡፡


ብሊንከን ሩሲያ ከቻይና የምታገኘውን ድጋፍ በዩክሬይኑ ጦርነት ጥቅም ላይ እያዋለችው ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ቻይና ሩሲያን መደገፏን እንድታቆም ጠይቀዋል፡፡


ቤጂንግ ሞስኮን መደገፏን ካላቆመች አሜሪካ የራሷን እርምጃ ታጤናለች ማለታቸውን ተሰምቷል፡፡


በቻይና ላይ የአሜሪካ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ብሊንከን አላፍታቱትም፡፡


የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቻይና ጉብኝት አድርገዋል፡፡


በአጋጣሚውም የቻይናው ፕሬዘዳንት ሺ ጂን ፒንግ ሁለቱ አገሮች ከትብብር እንጂ ከመቀናቀን የሚያተርፉት ነገር የለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



የየመን ሁቲዎች በሰነዘሩት የሚሳየል ጥቃት በአንዲት የንግድ መርከብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተሰማ፡፡


በመርከቧ ላይ ጥቃት የደረሰባት ሞካ ከተሰኘው የየመን የባህር ዳርቻ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


ነዳጅ መጫኛ መርከብ በስም ተለይታ አልተጠቀሰችም፡፡


በጊዜውም ወደ ህንድ በማምራት ላይ ነበረች ተብሏል፡፡


ሁቲዎቹ እስራኤል የጋዛ ዘመቻዋን አቁማ ካልወጣች በተባባሪዎቿ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳችንን አናቆምም በሚል አቋማቸው ገፍተውበታል፡፡


አሜሪካ እና ብሪታንያ ሁቲዎቹን ለማስታገስ በሚል በይዞታቸው ላይ ድብደባ እየፈፀሙ ነው፡፡


ሁቲዎቹ ግን ከአቋቸው ሽብረክ እንዳላሉ ይነገራል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram:  @ShegerFMRadio102_1




bottom of page