top of page

መጋቢት 3፣2016 - አምስት ተቋማት ለሰሩት የስኬት ስራ ተሸለሙ

ሽልማቱ የተሰጠው "የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት በሚል" ነው።


በአድዋ መታሰቢያ በተካሄደ ስነስርዓት የተሸለሙት የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ፖስታ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ናቸው።


የግብርና ሚኒስቴር ለሸልማት ያበቃው በስንዴ ምርት ከሀገር ፍጆታ አልፎ ለውጪ ገበያ የሚበቃ ምርት እንዲመረት በማስቻሉ ነው ተብሏል።


የ78 ዓመት እድሜ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላው አለም ያለው ከፍተኛ ተወዳዳሪነት ለሽልማት አብቅቶታል ተብሏል።


152 አውሮፕላኖች ያሉት አየር መንገዱ በተለይ በኮቪድ ወቅት የአለም አየር መንገዶች ሲቸገሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን አካሄዱን ከጊዜው ጋር አስማምቶ መስራቱ እንደ ከፍተኛ ስኬት ተነስቶለታል።


የግዙፍ የመንገደኞች ማስተናገጃ(ተርሚናል )፣ ግዙፍ የአውሮፕላን ጥገና እና ምግብ ማዘጋጃ ያሉት አየር መንገዱ በአሁኑ ሰዓት በአለም ዙሪያ 134 መዳረሻዎች እንዳሉት ተጠቅሷል።


በአፍሪካ 60፣ በሀገር ውስጥ 22 መዳረሻዎች እንዳሉትም ተነግሯል።


በስኬት ጎዳና ላይ እንዳለ የተነገረለት አየር መንገዱ በዚህም የስኬት ሽልማት ተበርክቶለታል።


የ130 ዓመቱ የኢትዮጵያ ፖስታ ኪሳራ ላይ ከነበረበት የዛሬ አምስት አመት ጉዞው በአሁኑ ሰዓት በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር አትራፊ ወደ መሆን መሸጋገሩ ተነግሯል።


በዚህም የኢትዮጵያ ፖስታ በሰራው ጠንካራ ሪፎርም ከአፍሪካም ከአለምም ተፎካካሪ ተቋም መሆኑ ተነግሮለታል።


በደንበኞችም፣ በገቢም በከፍተኛ እድገት ውስጥ እንዳለ የተነገረለት ኢትዮ ቴሌኮም ሌላኛው የኢትዮጵያ ተቋማት የስኬት ሽልማት የተበረከተለት ተቋም ነው።


5 ቢሊዮን ብር በየቀኑ የሚገላበጥበት ቴሌ ብር ከተጀመረ እስካሁን 1.9 ትሪሊዮን ብር እንደተገላበጠበት ተነግሯል።

ይሄንም ከፍተኛ ስኬት መሆኑ በፕሮግራሙ ላይ ሲነገር ሰምተናል።


ኩባንያ በአሁኑ ወቅት 75 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ግዙፍ ተቋም መሆኑ ተጠቅሷል።


የግንባታው መጠናቀቅ ከጫፍ መድረሱ የተነገረለት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሌላው ተሸላሚ ነው።


በአሁኑ ሰዓት 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ መያዙ የተነገረለት ግድቡ በሁለት ተርባይኖች ሀይል እየሰጠ እንዳለ ተነግሯል።


በግንባታ ሂደት አጋጥሞ የነበረው መዘግይት እና አሱን ተከትሎ የሲቪል ስራውን የሚሰራው ተቋራጭ ከፍተኛ ካሳ መጠየቁ ተነግሯል።


የሜቴክን ውል ማቋረጥን ጨምሮ የተወሰዱ እርምጃዎች የግድቡን ግንባታ ከጫፍ እንዲደርስ ማድረጉ ተነስቷል።

ለተቋማቱ የስራ ሀላፊዎች ሽልማቱን ያበረከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ናቸው።


ተቋማቱ ሽልማቱ የተበረከተላቸው በዋናነት ከለወውጡ ወዲህ ባስመዘገቡት ሪፎርም ብቻ ሳይሆን በአህጉር ደረጃ ባለቸው ስኬት መሰረት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።


ለተቋማቱ የተሰጣቸው ሽልማት ከዋንዛ እንጨት በቅጠል ቅርፅ የተሰራ ስጦታ ነው።



ንጋቱ ሙሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




bottom of page