top of page

መጋቢት 18፣2016 - ደመወዝ ሳያገኙ የቆዩና በትግራይ ይሰሩ የነበሩ የግል ድርጅት ሰራተኞች ጉዳይ የተለየ ውይይት ያስፈልገዋል ተባለ

በነበረው ጦርነት ምክንያት ደመወዝ ሳያገኙ የቆዩና በትግራይ ክልል ይሰሩ የነበሩ የግል ድርጅት ሰራተኞች ጉዳይ የተለየ ውይይት ያስፈልገዋል ተባለ፡፡


ከሰራተኞቹ መካከልም ለ 2 ዓመት ምንም ደመወዝ ያላገኙ መኖራቸውም ተነግሯል፡፡


ይህ እንዳሳሰበው ተናግሮ ‘’የሰራተኞቹ ችግር ለማቃለል ልዩ ውይይት ያስፈልጋል’’ ያለው የኢትጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን ነው፡፡


ምንም እንኳ በክልሉ ከጦርነቱ በኋላ ዳግም ስራ የጀመሩ ቢኖሩም፤ እስካሁን ስራ ያልጀመሩ ድርጅቶች በመኖራቸው ሰራተኞቹ በችግር ውስጥ እንዳሉ የኢሰማኮ ፐሬዚደንት ካሳሁን ፎሎ ለሸገር ተናግረዋል፡፡



‘’ችግሩ ዉስብስብ ስለሆነም ጉዳዩ መታየት ያለበት ከህግ አንፃር ብቻ ሳይሆን የተለየ ውይይት ያስፈለገዋል’’ ብለውናል ፕሬዚዳንቱ፡፡


‘’በጦርነት የወደመን ድርጅት ለሰራተኞች ደመወዝ ክፈል ማለት ከባድ በመሆኑ ከክልሉ እና ከሚመለከታቸው ጋር ምክክር ለማድረግ እየሞከርን ነው’’ ሲሉም አውርተውናል፡፡


‘’በአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት የድርጅት ትርፋማነትን ተንተርሶ ነው ለሰራኞች ደመወዝ የሚከፈለው’’ የሚሉት አቶ ካሳሁን ሰራተኞቹ ደመወዝ ያልተከፈላቸው መቼ እና ድርጅቱ በምን አይነት ሁኔታ ዉስጥ እያለ ነው የሚለው ሊታይ የሚገባ ነውም’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ከዓመት በላይ ደመወዝ ሳይከፈላቸው የቆዩና በትግራይ ክልል ያሉ የመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች ጉዳይ መንግስት በፖለቲካዊ ውሳኔ ደመወዛቸውን ለመክፈል ወስኛለሁ ብሎ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ከቀናት በፊት ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡



ማንያዘዋል ጌታሁን



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




bottom of page