top of page

ኢትዮጵያ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ጋር በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ ደርሳበት የነበረው የብድር ሽግሽግ ሳይሳካ ቀረ፡፡

  • sheger1021fm
  • 12 minutes ago
  • 1 min read

ጥር 22/2018


ኢትዮጵያ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ጋር በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ ደርሳበት የነበረው የብድር ሽግሽግ ሳይሳካ ቀረ፡፡


የብድር ሽግሽጉን በተመለከተ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ጠበቃ ቀጥራ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ጋር ንግግር ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል፡፡


ከሳምንታት በፊትም በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አሳውቀው ነበር፡፡


ይሁንና ስምምነታቸው ስራ ላይ ይውል ዘንድ የአለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት IMF እና የቡድን 20 ሃገራት የአበዳሪዎች ኮሚቴ ይሁንታ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡


ታዲያ የቡድን 20 ሃገራት የአበዳሪዎች ኮሚቴ እንዳለው ኢትዮጵያ ከወጭ ንግድ የምታገኘው ገቢ IMF ከተነበየው በላይ ከሆነ ከምታገኘው ገቢ 2 ነጥብ 75 በመቶ ለዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች በተጨማሪነት እንድትከፍል የሚጠይቀው የስምምነት አካል ኢትዮጵያ ብትስማማበትም የጂ 20 የአበዳሪዎች ኮሚቴ ግን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡


ይህንንም ኮሚቴው ለኢትዮጵያ በፃፈው ይፋዊ ደብዳቤ አሳውቋል፡፡


በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ ተደርሶበት የቆየው የብድር ሽግሽግ የሁሉንም አበዳሪ አገሮችን እኩል የመመልከት እሳቤን ያላከበረ ነው ብሎታል፡፡


በመሆኑም በፈረንጆቹ 2024 መከፈል የነበረበትና ኢትዮጵያ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች የወሰደችው፤ ሳትከፍለውም የቆየችው የ1 ቢሊዮን ዶላር እዳ ሽግሽግን በተመለከተ ሲደረግ የቆየው ረዥም ንግግር ሳይሳካ ቀርቷል፡፡


እንደ አዲስም ኢትዮጵያ የእዳ ሽግሽጉን ልትጀምር ትችለላች የተባለ ሲሆን ይህን ስታደርግም ከIMF ጋር የገባችበትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሆዎችን ባልጣሰ መልኩ መሆን አለበት መባሉን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡


ኢትዮጵያ ከዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ያለባት የ1 ቢሊዮን ዶላር እዳ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት የወሰደችው ነበር ተብሏል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page