top of page

መጋቢት 18፣2016 - "የኛ ማይክሮ ፋይናንስ" ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ወጣቶች በልዩ ሁኔታ ብድር እየሰጠ መሆኑን ተናገረ

የዛሬ ሁለት ዓመት ስራ የጀመረው "የኛ ማይክሮ ፋይናንስ" ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ወጣቶች በልዩ ሁኔታ ብድር እየሰጠ መሆኑን ተናገረ።


ከብት ለሚያደልቡ፣ ንብ ለሚያንቡ የከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩም በልዩ የብድር መንገድ ይስተናገዳሉ ተብሏል።


ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ብድር ከሌሎች አይነቶች ዝቅተኛ ወለድ የሚሰላበት እንዲሁም ንግድ ፍቃድ ባይኖራቸውም ተበዳሪዎቹ ስራቸውን በትክክል እየሰሩ መሆናቸው ከተረጋገጠ ብድር ይሰጣቸዋል ሲሉ የድርጅቱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ተጠባባቂ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ደራሽ በሀይሉ ለሸገር ነግረዋል።


የኛ ማይክሮ ፋይናንስ በሁለት ዓመት ቆይታው ለ500 ሰዎች ብድር ሰጥቻለሁ፣ ከ10,000 በላይ የቆጠቡ ደንበኞችም አሉኝ ብሏል።


ድርጅቱ በ40 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል እና በ10 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን አሁን ላይ የተከፈለ ካፒታሉ 160 ሚሊዮን ብር መድረሱን ሰምተናል።


የኛ ማይክሮ ፋይናንስ በሳምንት ሰባቱንም ቀናት እሰራለሁ፣ ለቀረበልኝ የብድር ጥያቄም መስፈርቱን ካሟላ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብድር እለቃለሁ ብሏል።


በአዲስ አበባ 3 ቅርንጫፎች እንዳሉት የተናገረው ድርጅቱ ወደ ክልልም ለማስፋት የአዋጭነት ጥናቱ እያለቀ መሆኑን አስረድቷል።



ንጋቱ ሙሉ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




bottom of page