top of page

መስከረም 9፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች



የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በሱዳን የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች በህፃናት ላይ እየደረሰ ያለው ሞት በእጅጉ አሳሳቢ ነው አለ፡፡


በመጠለያ ጣቢያዎቹ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ በበሽታ እና በከፋ የምግብ እጥረት ከ1 ሺህ 200 ያላነሱ ሕፃናት ሕይወት ተቀጥፏል ማለቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በአሁኑ ወቅት የኩፍኝ ወረርሽኝ በመጠለያዎቹ እየተስፋፋ ነው ተብሏል፡፡


በምግብ እጥረት ክፉኛ የተጎዱ ከ50 ሺህ ያላነሱ ሕፃናት አጣዳፊ ሕክምና እንደሚያሻቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


ከ5 ወራት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ ቀውሱን እያባባሰው መምጣቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡



በኬንያ ወታደራዊ የቅኝት ሔሊኮፕተር መከስከሱ ተሰማ፡፡


ብዛታቸው ባይጠቀስም በአደጋው በሒሊኮፕተሩ ተሳፍረው የነበሩ የጦር ባልደረቦች ሕይወት ማለፉ እንደተነገረ አናዶሉ ፅፏል፡፡


ሔሊኮፕተሩ የተከሰከሰው በላሙ ግዛት ቦኒ ደን ውስጥ መሆኑ ታውቃል፡፡


ጫካውን የሶማሊያው ፅንፈኛ ቡድን ለጥቃት መንደርደሪያነት ታጣቂዎቹን ሲሸሽግበት የቆየ መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡


ኬኒያ በአልሸባብ ፅንፈኛ ቡድን የድንገት ደራሽ ጥቃት ሲፈፀምባት መቆየቷ ይነገራል፡፡


የኬንያ ጦር ስለ ሔሊኮፕተሩ አደጋ ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫ መስጠቴ አይቀርም ማለቱ ተሰምቷል፡፡



የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በፀጥታው ምክር ቤት እና በሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት አጠቃላይ ማሻሻያ ልናደርግ ይገባል አሉ፡፡


ጥያቄው በተለያዩ አካላት እና ሀገሮች ሲስተጋባ የቆየ መሆኑን TRT ዎርልድ አስታውሷል፡፡


ዋና ፀሐፊው ማሻሻያ ሊደረግባቸው ያሻል ካሏቸው መካከል እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /IMF/ እና የአለም ባንክ ያሉ የፋናንስ ተቋማትም ይገኙበታል ተብሏል፡፡


ጉቴሬዝ የፀጥታው ምክር ቤት እና የፋይናንስ ተቋማቱ ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል ያሉት ለ78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር መሆኑ ታውቋል፡፡


የፖርቱጋሉ ፕሬዘዳንት ማርሲሎ ሬቤሎም ተመሳሳይ ጥያቄ ያዘለ ንግግር ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡



ፓኪስታን በሚስጥር ለዩክሬይን የጦር መሳሪያ እና ተተኳሾችን እያቀበለች መሆኑ ተሰማ፡፡


ይሄን ጉዳይ ለሚስጥሩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች መሰማቱን የፃፈው ሚድል ኢስት ሞኒተር ነው፡፡


ፓኪስታን ለዩክሬይን የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን የምታቀብለው በቅርቡ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /IMF/ ላገኘችው የምጣኔ ሐብታዊ መታደጊያ ገንዘብ ምላሽ ነው ተብሏል፡፡


IMF ለፓኪስታን ባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዱን ዘገባው አስታውሷል፡፡


ፓኪስታን ለዩክሬይን የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን እንድታቀብል የአሜሪካ ጫና እንዳለባት ተጠቅሷል፡፡


ያፈተለኩ ሰነዶችም በIMF ብድር እና ከፓኪስታን ለዩክሬይን በሚሰጠው የጦር መሳሪያ መካከል ግንኙነት እንዳለ ያሳያሉ ተብሏል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

bottom of page