top of page

መስከረም 24፣2016 - የቴሌኮም ማጭበርበር ሲፈፅሙ የተደረሰባቸው ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ


የቴሌኮም ማጭበርበር ሲፈፅሙ የተደረሰባቸው 30 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ።


ከ73 በላይ የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎችም ተይዘዋል ተብሏል።


ግለሰቦቹ በቁጥር ስር የዋሉት በአዲስ አበባ፣ ሸገር ከተማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ ሐዋሳ እና ጅማ ከተሞች መሆኑ ተነግሯል።


ግለሰቦቹ እና የተሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎቹ ሊያዙ የቻሉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በመተበበር እንዲሁም ከቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ባለሙያዎችና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ለሶስት ወራት በሰሩት ስራ መሆንን ሰምተናል።

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የግለሠብ ቤቶችንና ግቢዎችን በመከራየት ሲያጭበርብሩ ቆይተዋል የተባለ ሲሆን ለዚህም አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ከ200 ሺ በላይ የሳፋሪኮም እና ኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዶች መያዛቸውን ተነግሯል ፡፡


በቁጥጥር ስር ከዋሉ የማጭበርበሪያ ጌትዌይ መካከልም በአንድ ጊዜ 127 ሲም ካርድ መያዝ የሚችል መሣሪያ መገኘቱንም ተጠቁሟል፡፡


የሚፈጸመው የማጭበርበር ድርጊቶች ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ አስቀርቷል፤ ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ባለፉት ስድስት ወራት ከ500 ሚልዮን ብር በላይ ብር አሳጥቷል ተብሏል፡፡


መሣሪያዎቹ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው የተባለ ሲሆን፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ይሁን ከሳፋሪኮም ምንም እውቅና የሌላቸው ነገር ግን ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ኢትዮ ቴሌኮም ወይም ሳፋሪኮም በዘረጋው ኔትወርክ ሳይሆን ራሳቸው በዘረጉት የማጭበርበሪያ ጌትዌይ ለደንበኞች የሚያቀርቡ ነበሩ ተብሏል ፡፡

የማጭበርበሪያ መሣሪያዎቹ ከጎረቤት ሀገራት በድንበር በኩል እስከ መሀል ከተማ ድረስ የሚቀባበሉ ደላሎች፣ በርካታ የኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ሲም ካርድ እና ሞባይል ካርድ ለእነዚህ አጭበርባሪዎች የሚያደርሱ ተባባሪ ወንጀለኞች እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡


ተጠርጣሪዎች መቀመጫቸውን ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎች ሀገራት ካደረጉ ዜጎች ጋር በመመሳጠር እና ተቀጥረው በመሥራት ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደተደረሰባቸው ተጠቁሟል።

bottom of page