በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከግጭትና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ የንጹሃን ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ኢሰመኮ ተናገረ።
- sheger1021fm
- 2 hours ago
- 1 min read
ጥር 23/2018
በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከግጭትና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ የንጹሃን ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ኢሰመኮ ተናገረ።
ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስቧል ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከጥር 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን እየተከታተለ መሆኑን በመግለጫው ተናግሯል፡፡
በዚህም እስከ ትናንት ለሊት ድረስ በተለይም በጸለምት/ጠለምት፣ በመጋሌ እና አብአላ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎ የሰዎችን የሕይወት፣ የአካል ደኅንነት፣ ነጻነት እና ንብረት መብቶች ሥጋት ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በአካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ወደ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል የሚል ሥጋት በመፈጠሩ ሳቢያ ነዋሪዎች ‘በኮማንድ ፖስት’ ሲተዳደሩ ከቆዩት አላማጣ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ መሆኑን እንዲሁም በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ገደቦች መጣላቸውን ኢሰመኮ ተናግሯል ፡፡
ይህ ግጭት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በአካባቢዎቹ ሰፍኖ የነበረውን አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ወደ ኋላ የሚመልስ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ለተጨማሪ ጉዳት፣ መፈናቀል እና ለሌሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚያጋልጥ መሆኑኑ ኮሚሽኑ ተናግሯል።
በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ በሲቪል ሰዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን ከማድረስ እንዲታቀቡ የጠየቀው ኮሚሽኑ ለግጭት መነሻ የሆኑ ልዩነቶችን በሕግ መሠረት እና በምክክርና እንዲፈቱ አሳስቧል ።
ማናቸውም የሚወሰዱ እርምጃዎች እና ገደቦች የሰብአዊ መብቶች መርሆችን ያከበሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል ይገባል ብሏል ኢሰመኮ በመግለጫው።
ኢሰመኮ ከመደበኛው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራው በተጨማሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የተፈጠረው ግጭት በውይይት የሚፈታበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል።












Comments