መስከረም 23 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
- sheger1021fm
- Oct 3
- 2 min read
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሣ ለጋዛ ፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ በጀልባ ሲያመሩ በእስራኤል ጦር ተይዘው የታሰሩት በጎ ፈቃደኞች እንዲለቀቁ ጠየቁ፡፡
ከታሰሩት የብዙ አገሮች ዜጎች መካከል ደቡብ አፍሪካውያንም እንደሚገኙበት አናዶሉ ፅፏል፡፡
የእስራኤል ጦር በብዙ ጀልባዎች ተሳፍረው ወደ ጋዛ ሲያመሩ ከነበሩት በጎ ፈቃደኞች መካከል 500 ያህሉን ማሰሩ ተሰምቷል፡፡
40 ጀልባዎቻቸውም ወደ እስራኤል ወደቦች ተወስደዋል ተብሏል፡፡

ከአለም አቀፍ የውሃ አካል የተያዙት በጎ ፈቃደኞቹ ከብዙ የአለማችን አገሮች የተውጣጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሲሪል ራማፎሣ እስራኤል ደቡብ አፍሪካውያኑን ጨምሮ ሁሉንም በጎ ፈቃኞች እንድትለቅ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
እስራኤል በጎ ፈቃደኞቹን ያሰረችው የጋዛ የባህር ከበባዬን በህገወጥ መንገድ ለመጣስ ሞክረዋል ብላ ነው፡፡
በጎ ፈቃኞቹ በእስራኤል ተይዘው መታሰራቸው ከተለያዩ አገሮች ውግዘት እና ተቃውሞ አስከትሎባታል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር በዳርፉር ግዛት አልፋሻር ከRSF ሀይል ጋር ተሰልፈው የቆዩ የውጭ አገር ዜጎችን ገድያለሁ አለ፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር በኤልፋሻር ገድያቸዋለሁ ያለው የውጭ ቅጥረኛ ተዋጊዎች የኮሎምቢያ እና የዩክሬይን ዜጎች እንደሆኑ አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ አልተጠቀሰም፡፡
ከተገደሉ የውጭ ቅጥረኞች መካከል የሰው አልባ በራሪ አካላት ዘዋሪ ኢንጂኒየሮችም አሉበት ተብሏል፡፡
RSF ዩክሬይን ስሪት ድሮኖችን ለቅኝት እና ለጥቃት እየተገለገለ መሆኑን ጦሩ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይልም ሆነ ስማቸው በሱዳን መንግስት ጦር በክፉ የተነሳ አገሮች በዚህ ጉዳይ ያሉት ነገር የለም፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር ከRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጋር ሲዋጋ ከ2 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡
የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን(ሐማስ) በፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ጦርነቱን ለማስቆም ተነድፎ የቀረበውን እቅድ በጭራሽ እንደማይቀበለው ፍንጭ መስጠቱ ተሰማ፡፡
እቅዱ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እና በወደፊቱም የጋዛ ሰርጥ አስተዳደር ምንም ዓይነት ሚና እንዳይኖረው የሚጠይቅ መሆኑን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
በካታር የሚገኙ የሐማስ መሪዎች እቅዱን ከማሻሻያዎች ጋር የመቀበል አዝማሚያ እያሳዩ ነው ተብሏል፡፡
በጋዛ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪ እቅዱን ቡድናቸው ተቀብለው አልተቀበለው እኛን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የታለመ በመሆኑ እስከ መጨረሻው እንዋጋለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
እንደሚባለው የተወሰኑ የሐማስ መሪዎች በጋዛ አለም አቀፍ አረጋጊ ሀይል መሰማራቱንም እየተቃወሙት ነው፡፡
ሐማስ ሉአላዊነት ፍልስጤም ሕውልና ካላገኘች በስተቀር በጭራሽ ትጥቅ አልፈታም እያለ ነው፡፡
የጀርመኑ ሙኒክ ኤርፖርት አገልግሎት ለማቋረጥ ተገደደ ተባለ፡፡
ኤርፖርቱ አገልግሎቱን ያቋረጠው በኤርፖርቱ ሰማይ መነሻቸው ያልታወቀ በርካታ ድሮኖች ሲያንዣብቡ ከታዩ በኋላ ነው መባሉን AFP ፅፏል፡፡
ቀደም ሲል የዴንማርኩ ኮፐንሐገን ኤርፖርት እና በአውሮፓ የተለያዩ አገሮች መሰል ችግር አጋጥሟል ሲባል ሰንብቷል፡፡
በሙኒክ ኤርፖርት ማረፍ የነበረባቸው አውሮፕላኖች አቅጣጫ ቀይረው በኑረምበርግ በፍራክፈርት ፣ በቬየናና በሽቱትጋርት እንዲያርፉ ተደርጓል ተብሏል፡፡
የሙኒክ ኤርፖርት መቼ ወደ ሙሉ አገልግሎቱ እንደሚመለስ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
ቀደም ሲል የኖርዌይ ኦስሎ እና የፖላንድ ዋርሶ ኤርፖቶችም ተመሳሳይ ችግር ገጥሞን ነበር ማለታቸው መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments