top of page

መስከረም 22 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Oct 2
  • 2 min read

የኒጀር እና የማሊ ወታደራዊ መንግስታት በምክክር ላይ ናቸው ተባለ፡፡


የሁለቱ አገሮች ምክክር አስተናጋጅ ማሊ እንደሆነች አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


የኒጀሩ ወታደራዊ መንግስት መሪ ጄኔራል አብዱራሂማኔ ትቻኒ ለምክክሩ በማሊ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

ree

ሁለቱ አገሮች ቡርኪናፋሶን ጨምረው የሳሕል አገሮች የትብብር ጥምረት የተሰኘ ኮንፌዴራላዊ አካል እያበጁ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


አገሮቹ የመከላከያ ሀይሎቻቸውን የማቀናጀት ውጥን አላቸው ተብሏል፡፡


የጋራ የልማት ባንክ የማቋቋም ሀሳብ እንዳላቸው ታውቋል፡፡


ሶስቱ የሳህል ወታደራዊ መንግስታት አገሮቻቸውን ከምዕራብ አፍሪካ መንግስታት ምጣኔ ሐብታዊ ማህበር /ኤኮዋስ/ አባልነት አስወጥተዋል፡፡


በሳሕል የፅንፈኛ ታጣቂዎች ማየል የ3ቱም አገሮች ወቅታዊ የደህንነት ስጋት እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡



የኬንያ ፖሊስ በበርካታ የነፍስ ግድያዎች ተጠርጣሪ የሆነው ኮሊንስ ጁማይሲ ካሉሻ ያለበትን ለመራኝ የ1 ሚሊዮን ሺልንግ ወረታ እከፍላለሁ አለ፡፡


ፖሊስ እከፍላለሁ ያለው ወረታ የ7,700 ዶላር የምንዛሪ ግምት እንዳለው ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ግለሰቡ ከ40 በላይ ሴቶች ላይ በተፈፀመ ግድያ እንደሚፈለግ ተጠቅሷል፡፡


በብርቱ ብርቱ ወንጀሎች የሚፈለገው ካሉሻ ከአመት በፊት ተይዞ እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡


ሆኖም እንደተያዘ ብዙም ሳይቆይ ከፖሊስ እስር ቤት ማምለጡ ብዙ ኬኒያውያንን አስቆጥቶ ቆይቷል፡፡


የኬንያ ፖሊስ ተፈላጊው ከአመት በላይ መልሶ ሊይዘው አለመቻሉ ለትዝብት እንዳጋለጠው መረጃው አስታውሷል፡፡



የእስራኤል ጦር ሰብአዊ እርዳታ ጭነው ወደ ጋዛ ሰርጥ በማምራት ላይ የነበሩ እና በጎ ፈቃደኞች ከተሳፈሩባቸው ጀልባዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ከጉዟቸው አሰናከላቸው ተባለ፡፡


44 ጀልባዎች ከተሳፈሩባቸው በጎ ፈቃደኞች ጋር በእስራኤል ጦር ተይዘው ወደ አገሪቱ ወደብ መወሰዳቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ከተያዙት በጎ ፈቃደኞች መካከል በአካባቢው ጥበቃ ተሟጋችነቷ የምትታወቀው ሲውድናዊቱ ግሬት ተምበርግ ትገኝበታለች ተብሏል፡፡


ግሬታ ተምበርግ በእስራኤል ጦር መያዟን እስር ብቻ ሳይሆን እገታም ጭምር ነው ማለቷ ተሰምቷል፡፡


ብዙ አገሮች የእስራኤልን እርምጃ መኮነን እና ማውገዛቸው ተሰምቷል፡፡


የኮሎምቢያ እርምጃ ደግሞ ከውግዘትም ያለፈ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


የላቲን አሜሪካዋ አገር ለዚሁ የእስራኤል እርምጃ ምላሽ የእስራኤል ዲፕሎማቶች፤ በሙሉ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛቸዋለች ተብሏል፡፡


ኮሎምቢያ ከእስራኤል ጋር የነበራትን የነፃ ንግድ ስምምነት ሰርዣለሁ ማለቷን መረጃው አስታውሷል፡፡



በአሜሪካ የፌዴራሉ አስተዳደር መንግስታዊ አገልግሎት በአብዛኛው እየተስተጓጎለ ነው ተባለ፡፡


ችግሩ የተፈጠረው የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ /ሴኔት/ የወጪ አስተዳደር ሕጉን ባለማፅደቁ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


መንግስታዊው አገልግሎት መስተጓጎል የያዘው ዴሞክራቶቹ እና ሪፖብሊካውያን እንደራሴዎች በወጪ አስተዳደር ህጉ ላይ ባለመስማማታቸው ነው ተብሏል፡፡


ጉዳዩ በአጣዳፊ መፍትሄ ካልተበጀለት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል መንግስቱ ሰራተኞች ክፍያ በማይታሰብበት የግዳጅ እረፍት ሊሸኙ እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡


ለመንግስታዊው አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ለሆነው የወጪ አስተዳደር ህግ ያለመፅደቅ ዴሞክራቶቹ እና ሪፖብሊካውያኑ በአንተ ነህ ፤ አንተ ነህ መካሰስ ይዘዋል፡፡


ሕጉ በፍጥነት የሚፀድቅበት መላ ካልተፈለገ የአገልግሎት መቋረጡ ከቀናትም በላይ ሊዘልቅ እንደሚችል መገመቱን መረጃው አስታውሷል፡፡



የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን (ሐማስ) የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛውን ጦርነት ለማስቆም ባቀረቡት የሰላም እቅድ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግለት ይሻል ተባለ፡፡


የትራምፕ የጋዛ የሰላም እቅድ ሐማስ ታጋቾችን በሙሉ ከመልቀቅ በተጨማሪ ትጥቅ ፈትቶ የጦር መሳሪያዎቹን በሙሉ እንዲያስረክብ የሚጠይቅ ጭምር እንደሆነ TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡


በወደፊቱ የጋዛ አስተዳደርም ሐማስ ምንም ዓይነት ሚና እንዲኖረው አይፈቀድለትም ተብሏል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት በእቅዱ ላይ ተስማምተውበታል፡፡


AFP ለሐማስ መሪዎች ቅርበት ያላቸው ምርጮች ነግረውኛል እንዳለው ታጣቂው ቡድኑ ትጥቅ በመፍቻው ጉዳይ ማሻሻያ እንዲደረግለት ይሻል ተብሏል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ ያለ አንዳች መዘግየት እቅዱን እንዲቀበል ማስጠንቀቃቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page