top of page

ሐምሌ 23 2017 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Jul 30, 2025
  • 2 min read


በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ካምቻትካ የባህር ዳርቻ በእጅግ ከባድ ርዕደ መሬት ተመታ፡፡


ርዕደ መሬቱ በብዙ ስፍራዎች ጎርፍ ማስከተሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የካምቻትካን የባህር ዳርቻ የመታው ነውጥ በርዕደ መሬት መለኪያ (ሬክተር ስኬል) 8.8 ሆኖ መመዝገቡ ታውቋል፡፡


አካባቢው በታላቅ ርዕደ መሬት ሲመታ ከ73 አመታት በኋላ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡

እስከ 4 ሜትር ከፍታ ያለው የባህር ማዕበል ሱናሚ መቀስቀሱ ተሰምቷል፡፡


በዚህም ምክንያት አሜሪካ እና ጃፓንን ጨምሮ በብዙ አገሮች የሱናሚ አደጋ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ታውቋል፡፡


ፊሊፒንስ ፣ ኢንዶኔዥያ ፣ ጉአም ፣ ፔሩ እና ኢኳዶር ማስጠንቀቂያ ከተሰጠባቸው መካከል ናቸው፡፡


በጃፓን እና በአሜሪካ እንደ ሐዋይ ካሉ ስፍራዎች የባህር ዳርቻ ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ መታዘዛቸው ተሰምቷል፡፡



በስልጣን ላይ የሚገኙት የኮትዲቭዋር ፕሬዘዳንት አላሳን ዋተራ ለ4ኛ ጊዜም በፕሬዘዳንትነት እወዳደራለሁ አሉ፡፡


ዋተራ ለዚህ እንዲያመቻቸውም ቀደም ሲል ለፕሬዘዳንቱ የስልጣን ዘመን ገደብ የሚበጀውን ህገ መንግስት እንዳስቀየሩት አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


ፕሬዘዳንቱ ለመጪው ምርጫ እጩ ሆኜ እቀርባለሁ ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ጤንነቴም ይፈቅድልኛል ብለዋል ዋተራ፡፡


በፕሬዘዳንታዊ ምርጫው ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የነበሩት ቲያን ቲያም በምርጫ ኮሚሽኑ እና በፍርድ ቤት ውሳኔ ከፉክክሩ ውጭ መደረጋቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡


ቲያ ከፉክክሩ ውጭ የተደረጉት የፈረንሳይም ድርብ ዜግነት አላቸው በሚል ምክንያት ነው፡፡


እሳቸው ግን የፈረንሳይ ዜግነቴን ትቼዋለሁ ባይ ናቸው፡፡


ጉዳዩ በአገሪቱ ውጥረት ማንገሱ ይነገራል፡፡



ብሪታንያ ለፍልስጤም የነፃ አገርነት እውቅና ለመስጠት ለእስራኤል ቅድመ ሁኔታ አቀረበችላት፡፡


እስራኤል በአፋጣኝ በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም ካላደረገች ብሪታንያ ለፍልስጤም ነፃ አገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪየር ስታርመር መናገራቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የጋዛው የተኩስ አቁም ጥያቄ ካልተመለሰ ብሪታንያ በመጪው መስከረም ወር ከሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በተጓዳኝ ለፍልስጤም ነፃ አገርነት እውቅና ትሰጣለች ተብሏል፡፡


ፈረንሳይም ቀደም ሲል ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለፍልስጤም ነፃ አገርነት እውቅና እንደምሰጥ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናግረዋል፡፡


ፍልስጤም እስካሁን በ139 አገሮች የነፃ አገርነት እውቅና ማግኘቷን መረጃው አስታውሷል፡፡



በዩክሬይን እድሜያቸው ከ60 አመት በላይ የሆነ አዛውንቶች በውትድርና እንዲመለመሉ የሚያስችል ህግ ስራ ላይ ዋለ፡፡


የዩክሬይን ጦር በወታደሮች እጥረት ሲፈተን መቆየቱን AFP አስታውሷል፡፡


አሁን ግን በአገሪቱ ከ60 አመት በላይ የሆናቸው ዜጎች በውትድርና ተመልምለው እንዲያገለግሉ የሚፈቅድ ህግ በፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ መፈረሙ ተሰምቷል፡፡


አዛውንቶቹ ተመልማዮች በቅድሚያ ብቁ ስለመሆናቸው የጤንነት ምርመራ ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡


የጤና ምርመራውን የሚያልፉት ለ1 አመት በውትድርና ለማገልገል ውለታ እንደሚፈርሙ ታውቋል፡፡


አብዛኞቹም አዛውንቶቹ ተመልማዮች ከውጊያ ውጭ በሆኑ ወታደራዊ ተግባራት ተመድበው እንዲያገለግሉ እንደሚደረግ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡



በኮንጎ ኪንሻሣ የM 23 ታጣቂ ቡድን በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ተጨማሪ ሁለት ስፍራዎችን ያዘ ተባለ፡፡


አማጺ በድኑ በሰሜናዊ ኪቡ ግዛት ንጉሉሉ እና ንዴት የተባሉ ስፍራዎችን የያዘው ከኮንጎ ኪንሻሣ መንግስት ጋር ከሳምንት በፊት በበካታር ዶሃ የመርህ የሰላም መግለጫ መፈረሙን ተከትሎ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡


የካታሩ ሰነድ የተኩስ አቁምንም የሚጨምር ነው ተብሏል፡፡


የሰላም የመርህ መግለጫው ቢፈረምም እስካሁን ውጊያው እንዳልቆመ ተጠቅሷል፡፡


M 23 አማጺ ቡድን በጎረቤት ሩዋንዳ እንደሚረዳ እና እንደሚደገፍ ይነገራል፡፡


ሩዋንዳም በፊናዋ ከኮንጎ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሟን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page