ሐምሌ 18 2017 - ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመችው እቅድ እንዲሳካ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርቷ፤ ከ13 በመቶ በላይ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋታል ተባለ
- sheger1021fm
- Jul 25
- 2 min read
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት ያለመችው እቅድ እንዲሳካ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ሀገራዊ ምርቷ፤ ከ13 በመቶ በላይ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋታል ተባለ፡፡
ለዚህም ከፍተኛ ገቢ መሰብሰብ አለባት የተባለ ሲሆን በህገወጥ መንገድ የገንዘብ ማሸሽ ወንጀል ግን ፈተና ሆኖባት ቀጥሏል ተብሏል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ሰነድ እንዳለው ኢትዮጵያ ከ5 ዓመት በኋላ በ2030 የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት የያዘችው ውጥን እንዲሳካ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ሃገራዊ ምርቷ 13.2 በመቶ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋታል ብሏል፡፡
ለዚህም ከታክስ የምትሰበስበው ገቢ ከፍተኛው የገቢ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል የጠቀሰው ባንኩ የተለያዩ ፈተናዎች መኖራቸውንም ተናግሯል፡፡

በቂ ገቢ እንዳትሰበስብ ምክንያት ይሆናሉ ከተባሉት መካከል በህገወጥ መንገደፍ ገንዘብ ማሸሽ አንዱ ሆኖ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በህገወጥ መንገድ በሚሸሽ ገንዘብ ኢትዮጵያ ከምታጣው ሀብት እስከ 80 በመቶው አስመጭና ላኪዎች ገቢና ወጫቸው ላይ ሆን ብለው በሚፈጥሩት መዛነፍ ምክንያት የሚከሰት ነው ተብሏል፡፡
ከኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ለማሸሽ ዋናዎቹ መንገዶች ተብለው በሪፖቱ ከሰፈሩት መካከል ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገባ ምርት ከተገዛበት በላይ የተጋነነ ዋጋ ማቅረብ እና ወደውጭ ለሚላክ ምርት ደግሞ አነስተኛ ገቢ ወይም ዶላር እንደተገኘ አድርጎ ማቅረብ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡
በዚህም መንገድ ከ6 እስከ 23 በመቶው የሚደርሱ ግብይቶች ገንዘብ በህገወጥ መንገድ የሚሸሽባቸው ናቸው ተብሏል፡፡
ይህም መንግስትን እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ገቢ ያሳጣዋል ይላል የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት፡፡
በመሆኑም ያለመችውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ገቢ መሰብሰቡ ህገ-ወጥ አሰራሮችንም መልክ በማስያዙ እንድትበረታ ተመክራለች፡፡
በሌላም በኩል ከግብር ከሚገኝ ገቢ ባሻገር ኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፏንም በማሳደግ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰራች መሆኑን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡
ይሁንና በበቂ ሁኔታ በዘርፉ ላይ ኢንቨስት አለመደረጉንና የማዕድን ዘርፉም የታለመውን ያህል ገቢ እያስገኘ እንዳልሆነ አብራርቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ማዕድን ከአጠቃላይ ከወጭ ንግዱ ያለው ድርሻ 14 በመቶ ነው ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርቷ 10 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው እቅድ ያላት ቢሆንም እስካሁን ግን ድርሻው ከአንድ በመቶ ፈቀቅ ያለ አይደለም ተብሏል፡፡
ህገወጥ የማዕድን ቁፋሮም ዘርፉን አንቀው ከያዙ ፈተናዎች መካከል አንዱ መሆኑ በአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments