top of page

ህዳር 9 2018 -የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 54 minutes ago
  • 2 min read

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ለሳውዲ አረቢያ ዘመን አፈራሾቹን F 35 የጦር ጄቶች እንደምትሸጥ ፍንጭ ሰጡ፡፡


ቀደም ሲል አሜሪካ F 35 የጦር ጄቶች በአረብ አገሮች እጅ እንዲገቡ ፍላጎት እንዳልነበራት አልጀዚራ ፅፏል፡፡


አሁን ግን ትራምፕ ለሳውዲ F 35 የጦር ጄቶችን እንሸጥላታለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ሳውዲዎች ታላቅ አጋሮቻችን ናቸው ይሄንንም እናደርገዋለን ብለዋል ትራምፕ፡፡

ree

ትራምፕ የአብርሃም ስምምነቶች በሚሰኘው ማዕቀፍ ሳውዲ አረቢያ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድትመሰርትላቸው ይሻሉ ተብሏል፡፡


ሳውዲ አረቢያ ግን ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመመስረቴ አስቀድሞ የፍልስጤማውያን ነፃ መንግስት በሚቋቋምበት መላ አስተማማኝ ዋስትና ማግኘት እሻለሁ እያለች ነው፡፡


ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሳውዲው አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር በዋይት ሐውስ ሲነጋገሩ ትልቁ ጉዳይ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡



ኬፕ ቬርዴ ፣ ሞሪሺየስ እና ሲሼልስ ታላቅ የጤና ስኬት ማስመዝገባቸውን የአለም የጤና ድርጅት አበሰረ፡፡


ሶስቱ ደሴታማ የአፍሪካ አገሮች የኩፍኝ በሽታን ማጥፋታቸውን የአለም የጤና ድርጅት ማብሰሩን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ኬፕ ቬርድ ፣ ሞሪሺየስ እና ሲሼልስ ለዚህ ስኬት የበቁት ለ36 ተከታታይ ወራት አንድም በበሽታው የተያዘ ሰው ባለመገኘቱ ነው ተብሏል፡፡


ከዚህ ስኬት ለመድረስም ሶስቱ አገሮች ከሰሐራ በስተደቡብ የአፍሪካ ክፍል የመጀመሪያዎቹ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡


ጥብቅ የወረርሽኙን መከላከያ መላ እና ሰፊ የክትባት መርሐ ግብርን ስራ ላይ ማዋላቸው ለዚህ ስኬት እንዳበቃቸው ታውቋል፡፡


ጉዳዩን ሲከታተል የቆየ ኮሚሽንም እንዳረጋገጠላቸው የአለም የጤና ድርጅት እወቁት ማለቱን መረጃው አስታውሷል፡፡



የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በጋዛ ሰርጥ ሰላም ማስፈኛ ነው የተባለውን የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕን ባለ 20 ነጥቦች እቅድ አፀደቀ፡፡


እቅዱ በጋዛ አለም አቀፍ አረጋጊ ነው የተባለ ሀይል እንዲሰፍር ጭምር የሚጠይቅ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


አረጋጊው ሀይል ከግብፅ እና ከእስራኤል እንዲሁም አዲስ ከተቋቋመው የጋዛ ፖሊስ ጋር በትብብር ይሰራል ተብሏል፡፡


የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይ ውሳኔው ለጋዛ ሰርጥ አስቀድሞ የተደረሰው የተኩስ አቁም እንዲፀና እና እንዲዘልቅ ያግዛል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ግን የፀጥታውን ምክር ቤት ውሳኔ የተቃወመው ወዲያውኑ ነው፡፡


ሐማስ ውሳኔው የፍልስጤማውያንን መብት እና ፍላጎት ያላከበረ ነው ብሎታል፡፡


ውሳኔው በ13 አገሮች ሲደገፍ ሩሲያ እና ቻይና ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡



የደቡብ አሜሪካዋ አገር ኢኳዶር የተደራጀ የአደገኛ እፅ አስተላላፊ ቡድን ሎስ ላቦስ መሪ ነው የተባለው ዊልመር ቻቫሪያ ስፔን ውስጥ መያዙ ተሰማ፡፡


ግለሰቡ ፒፖ በሚል ቅፅል እንደሚታወቅ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ግለሰቡ ከ4 አመታት በፊት በኮቪድ 19 በሽታ ምክንያት እንደሞተ አድርጎ ራሱን ሸሽጎ መቆየቱ ተጠቅሷል፡፡


ፒፖ ሲመራው የቆየው የአደገኛ እፅ አስተላላፊዎች የተደራጀ የወንጀል ቡድን በኢኳዶርም ሆነ በአሜሪካ በሸባሪነት የተፈረጀ ነው ተብሏል፡፡


ኢኳዶር ከቅርብ አመታት ወዲህ ከዋነኞቹ የአደገኛ እፅ ማስተላለፊያዎች አንዷ እየሆነች መምጣቷ ይነገራል፡፡


የተለያዩ ተቀናቃኝ ቡድኖች የወንጀል መራኮቻ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡



በናይጀርያ ኬቢ ግዛት አንድ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 25 ሴት ተማሪዎች በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸው ተሰማ፡፡


ታጣቂዎቹ ትምህርት ቤቱን በወረሩበት ወቅት አካባቢውን በከባድ ተኩስ አሸብረውት እንደነበር አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡


የትምህርት ቤቱን ምክትል ርዕሰ መምህር መግደላቸው ተሰምቷል፡፡


የግዛቲቱ ፖሊስ ታጋች ሴት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ በአሰሳ ላይ ነኝ ብሏል፡፡


አጋቾቹ በደፈናው ታጣቂዎች ናቸው ከመባላቸው ውጭ የትኛው ድርጅት ታጣቂዎች እንደሆኑ አልተጠቀሰም፡፡


ከ11 አመታት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴት ተማሪዎች ከቺቦክ አዳሪ ትምህርት ቤት በቦኮ ሐራም ፅንፈኛ ታጣቂ ቡድን ታግተው መወሰዳቸው የአለምም መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል፡፡


የኔነህ ከበደ

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page