በናይጀርያ በነዳጅ ማጓጓዣ ቦቴ ላይ በደረሰ ፍንዳታ እና ቃጠሎ የ90 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡
አደጋው የደረሰው በሰሜናዊ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍል ነው፡፡
የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴው አደጋው የገጠመው በካኖ ሐዴጂያ የፍጥነት መንገድ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
ቃጠሎው ከባድ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በናይጀሪያ በተደጋጋሚ የቦቴዎች ቃጠሎ ይደርሳል፡፡
በሰሜናዊ ምስራቅ ናይጀሪያ የአሁኑ አደጋ በምን ምክንያት እንደደረሰ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱን ሁኔታ እንድታሻሽል አሜሪካ የ30 ቀናት የጊዜ ገደብ አስቀመጠችላት ተባለ፡፡
እስራኤል በዚህ ጊዜ በጋዛ ለፍልስጤም ሰላማዊ ነዋሪዎች የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱን ሁኔታ ካላሻሻለች አሜሪካ ለእስራኤል የምሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ እቀንሳለሁ ማለቷን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል ሰብአዊ ቀውሱ በእጅጉ ከከፋ ደረጃ መድረሱ ተጠቅሷል፡፡
እስራኤል በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል ወደ ዳግም የጦር ዘመቻ ተመልሳለች፡፡
አገሪቱ ዘመቻዬ በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል በየዋሻው ውስጥ ያሉትን የሐማስ ታጣቂዎች ለመደምሰስ ያለመ ነው ብላለች፡፡
የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ የተሰማው ወደ ምርጫዋ በተቃረበችበት ወቅት ነው፡፡
ከአመት በላይ በሆነው የእስራኤል የጋዛ ዘመቻ የተገደሉት ፍልስጤማውያን ብዛት ከ42 ሺህ በብዙ መብለጡ ተነግሯል፡፡
አብዛኞቹም የዘመቻው ሟቾች ሰላማዊ ሰዎች ናቸው ይባላል፡፡
የሊባኖሱ የጦር ድርጅት (ሔዝቦላህ) በቀጠናው ግጭት እንዲያበቃ እስራኤል በጋዛ ተኩስ ልታቆም ይገባል አለ፡፡
ጥያቄውን ያቀረቡት የሄዝቦላህ ምክትል መሪ የሆኑት ናይም ካሴም እንደሆኑ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
የሄዝቦላህ መሪ ሆነው የቆዩት ሐሰን ናስረላህ እስራኤል በፈፀመችው የአየር ድብደባ መገደላቸው ይታወቃል፡፡
እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ በተጨማሪ በሊባኖስም ከባድ የጦር ዘመቻ ከጀመረች ሰንብታለች፡፡
ሔዝቦላህም በእስራኤል ላይ የሮኬት እና የድሮን ጥቃት እየፈፀመ ነው ይባላል፡፡
ቡድኑ የኢራን ሁነኛ የጦር አጋር እና የፖለቲካ ሸሪክ መሆኑ ይነገራል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪዎች ጉዳይ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁን መረር ያለ አስተያየት ሰጡባቸው፡፡
እስራኤል ሰሞኑን በደቡብ ሊባኖስ ሰፍሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪዎች የጥበቃ ይዞታ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት መፈፀሟ ሲነገር ሰንብቷል፡፡
በዚህም 5 ሰላም አስከባሪ ወታደሮች አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው አረብ ኒውስ አስታውሷል፡፡
በዚያ ላይ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሰላም አስከባሪው በአፋጣኝ ከስፍራው ለቅቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ አገራቸው የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ ውጤት እንደሆነች ሊዘነጉት አይገባም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ማክሮን አስተያየቱን የሰጡት በኤሊሴይ ቤተ መንግስት በዝግ በተካሄደ ስብሰባ ወቅት አንደሆነ አንድ ተሳታፊ መናገራቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
#ቤኒያሚን ኔታንያሁ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ አገራቸው በኢራን ላይ የምትወስደውን ወታደራዊ እርምጃ በተመለከተ የአሜሪካን ምክር ብትሰማም አጠቃላይ ውሳኔዋ ብሔራዊ ጥቅሟን ያስጠበቀ እና የራሷ ይሆናል አሉ፡፡
ቀደም ሲል ዋሽንግተን ፖስት ኔታንያሁ የኢራንን የነዳጅ ዘይት አውታሮች እና የኒኩሊየር ተቋማት እንዳይመቱ በአሜሪካ ተመክረዋል የሚል ዘገባ ይዞ መውጣቱን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ኔታንያሁ ግን የምንመታውን ለይተን እናውቃለን በራሳችን እንወስናለን የሚል ዓይነት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኢራን ከ2 ሳምንታት በፊት በእስራኤል ላይ 180 ሚሳየሎችን መተኮሷን መረጃው አስታውሷል፡፡
ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስራኤል የአፀፋ ጥቃት መፈፀሟ አይቀርም ሲባል ሰንብቷል፡፡
በቀጠናው የጦርነቱ ስጋት አልተቃለለም፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments