top of page

ሚያዝያ  30፣2016 ‘’የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት’’ በኢትዮጵያ ስራ ላይ ማዋል ቀላል አይሆንም ተባለ

የታሪፍ ቅነሳ እና የውድድር ጫና ተፅዕኖ አለው የሚባለውን ‘’የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት’’ በኢትዮጵያ ስራ ላይ ማዋል ቀላል አይሆንም ተባለ።

 

የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ይህንኑ አውቀው ለውድድሩ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ተመክረዋል።

 

የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በዚሁ ዙሪያ ያዘጋጀው ውይይት ተካሂዷል።

 

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት፤ ከስድስት ዓመት በፊት በ44 የአህጉሩ ሀገራት መፈረሙ ይታወሳል።

 

ስምምነቱ በዋናነት በገቢ ዕቃዎች ላይ የሚጣለውን 90 በመቶ ታሪፍ ማስቀረት በአገልግሎት ንግድ ዙሪያ ያሉ ማነቆዎችን የመቀነስ ግብ አለው፡፡

 

1.3 ቢሊየን የሚሆኑ የአፍሪካን ህዝቦች በማቀራረብ፤  3.4 ትሪሊየን ዶላር ግምት የሚሆን አህጉራዊ ገበያን የሚፈጥር ስምምነት እንደሚሆንም ተስፋ ተደርጓል።

 

ከዚህ ስምምነት ቀዳሚ ፈራሚዎች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ለተግባራዊነቱ በዝግጅት ላይ ነች።

ይሁን እንጂ ስለዚህ ስምምነት አጠቃላይ ይዘት እና አተገባበር ያለው መረዳት በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ፤ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሠንበት ሸንቁጤ ተናግረዋል፡፡

 

በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ ስለዚሁ ስምምነት ተረድቶ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡   

 

በተለይ በኢትዮጵያ ነጻ ገበያ እና በአለም አቀፍ ንግድ ዙሪያ ያሉ ልምዶች አነስተኛ መሆናቸው ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረጉ ሂደት ፈተና ይሆናሉ ከተባሉ መካከል ናቸው፡፡

 

ስለ ስምምነቱ መረጃ ማግኘት፤ ከፍተኛ የሆነውን ኢ መደበኛ ንግድ ወደ መደበኛ ማስገባት እና፤ በኢንዱስትሪዎች ስራ ላይ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ማስወገድ ወይዘሮ መሠንበት መፍትሄ ብለው ከጠቀሷቸው መካከል ናቸው።

 

በጎርጎርሳውያኑ 2018 የተፈረመው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ከ2021 ጀምሮ በተወሰኑ ሀገራት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

 

ንጋቱ ረጋሣ

  

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

 

Comments


bottom of page