ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው የዋጋ ግሽበቱ ነጠላ ድጅት እስኪደርስ ድረስ ይቀጥላል ተባለ፡፡
- Dec 30, 2025
- 2 min read
ታህሳስ 21/2018
ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው የዋጋ ግሽበቱ ነጠላ ድጅት እስኪደርስ ድረስ ይቀጥላል ተባለ፡፡
ይህም የባንኮች የብድር አሰጣጥ ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጥሎ የቆየው ገደብ እንደሚቀጥል ያሳያል፡፡
ባንኮች ለአስቀማጮች ይሰጡት የነበረው የ7 በመቶ ወለድ በብሔራዊ ባንክ የተወሰነ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሁን ባንኮች እና ቆጣቢዎች እንዲደራደሩበት ወይም ለገበያው እንዲተው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ወስኗል፡፡
በብሔራዊ ባንክ ስር የተቋቋመ የገንዘብ ፖሊስ ኮሚቴ ዛሬ አምስተኛ ዙር ስብሰባውን አካሂዶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ለዛሬ ስብሰባውም የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው የተለያዩ 4 ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የብሄራዊ ባንክ የ15 በመቶ የፖሊሲ ተመን ባለበት እንዲቀጥል የሚለው የመጀመሪያው ውሳኔ ነው፡፡

በሌላ በኩል ኮሚቴው በባንኮች ያለው የጥሬ ገንዘብ ክምችት ከፍ ያለ በመሆኑ የባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየው 24 በመቶ ዓመታዊ የብድር እድገት ገደብ እስከመጭው ሶስት ወር እንዲቀጥል ወስኗል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት ባንኮች የሰጡት አዲስ ብድር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ያለው ኮሚቴው እንዲሁም በባንኮች ያለው የብድር ክምችት ከፍ ያለ መሆኑን ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
ይህም ወደ ገበያው የሚወጣውን ገንዘብ መጠን እንዲጨምር እያደረገ በመሆኑ ባንኮች በአስገዳጅነት በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የሪዘርቭ ምጣኔ ከአምስት ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲል ኮሚቴው ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠው ዝቅተኛ የቁጠባ ወለድም ቁጠባን ለማበረታታት ሲባል ዝቅተኛ የወለድ ተመንን ለገበያው እንዲተው ወይም በባንኮች እና በቆጣቢዎች መካከል በሚደረግ ድርድር እንዲወሰን ምክረ ሀሳብ ቀርቦ በቦርዱ ፀድቋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ከጥብቅ የግዘብ ፖሊሲው ባሻገር ብሔራዊ ባንክ ዋጋን ለማረጋጋት ሲባል ያሉትን የፖሊሲ አማራጮች ሁሉ እንዲጠቀም ኮሚቴው ወስኗል፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ እንዳለው ዛሬ በሚጠናቀቀው የፈረንጆች 2025 ዓመት የዋጋ ግሽበቱ ወደ 10.9 በመቶ ወርዳል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በያዘው እቅድ መሰረት ወደ ነጠላ ዲጅት እስኪደርስ ድረስም ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው ይቀጥላል ተብሏል፡፡
የምግብ የዋጋ ግሽበት ከአመት በፊት ከነበረበት 18.54 በመቶ ወደ 10.6 በመቶ ዝቅ ብሏል የተባለ ሲሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች የግሽበት ምጣኔ 11.4 በመቶ ነው ተብሏል፡፡
የሃገሪቱ አጠቃላይ ምርት እድገት ባለፉት 8 ዓመታት በአማካይ ከነበረበት የ7.5 በመቶ እድገት በ2025 ወደ 9 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ ማለቱም ተነግሯል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
Telegram : https://t.me/ShegerFMRadio102_1
Facebook፡ https://web.facebook.com/Sheger102.1





Comments