top of page

ጥቅምት 6 2018 - “የግዕዝ ቋንቋ በትምህርት ስርዓት ውስጥ”

  • sheger1021fm
  • Oct 16
  • 5 min read

የግዕዝ ቋንቋ በአማራ ክልል በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሰጠት በዚህ ዓመት ተጀምሯል፡፡


ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ መነጋገሪያ ወጥቶታል፡፡


አንዳንዶች እስይ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ አስፈላጊ አይደለም ልጆቻችንም አይማሩም ሲሉ ተሰምተዋል፡፡


ቀሪዎቹ ደግሞ በቋንቋ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ባያነሱም ከስንተኛ ከፍል ጀምሮ ነው ቋንቋው ለተማሪዎች መሰጠት ያለበት በሚለው ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡


“የግዕዝ ቋንቋ በትምህርት ስርዓት ውስጥ” በሚል ርዕስ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት በርካታ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተሳታፊዎች በተገኙበት ውይይት ተካሄዷል፡፡


በስነ ልሳን መምህሩ እና ተመራማሪው ዘላለም ልየው(ፕ/ሮ) አወያይነት፤ በበድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) እና በይኩኖአምላክ መዝገቡ መካከል ውይይት ተደርጓል፡፡

ree

የግዕዝ ቋንቋ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ስላለው አስፈላጊነት እና ከስንትኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጥ በሚለው ጉዳይ ላይ ተወያዮቹ የየራሳቸውን ሃሳብ ሰንዝረዋል፤ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል፡፡


በግዕዝ ቋንቋ አስፈላጊነት ላይ በስነ ልሳን መምህሩ በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) እና በግዕዝ ቋንቋ ተመራማሪው አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ መካከል ልዩነት የለም፡፡ ለስነ ጽሁፍ፣ ለስነ ከዋክብት፣ ለግብርና፣ ለባህላዊ ህክምና፣ታሪክን ለመረዳት እና ለምርምር አገልግሎት ቋንቋው ባለው አቅም ይስማማሉ።


የግዕዝ ቋንቋ በትምህር ስረዓት ወስጥ ተካትቶ ከስንተኛ ከፍል ጀምሮ ይሰጥ በሚለው ግን ይለያያሉ።


በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ቢሰጥ ሲሉ አቶ ይኩኖአምላክ በበኩላቸው ተማሪዎች በደንብ ቋንቋዉን እንዲይዙት ከ4ኛ እስክ 8ኛ ክፍል ቢሰጥ እና ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ በምርጫ እና በፍላጎት ቢሆን ሲሉ ሃሳባቸው አጋርተዋል።


በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) የግዕዝ ቋንቋ አሁን የሃይማኖት ቋንቋ ብቻ መሆኑ አስረድተው፤ አንድ ቋንቋ በስነ ልሳን ሞቷል የሚባለው ምን ሲሆን ነው? የሚለውን ሲያብራሩ አንድ ቋንቋ ተናጋሪው ከ25,000 በታች ሲሆን አደጋ ውስጥ ያለ ቋንቋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአፍ መፍቻ ተናጋሪ ማህበረሰብ ሲያጣ ደግሞ ሞቷል እንደሚባል በለሙያው ጠቁመዋል፡፡

ree

በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) የግዕዝ ቋንቋ ላይ የሚሰራ ኮሚቴ ወይም ማህበር አቋቁሞ የመናገሪያ ቋንቋ እናደርገዋለን ማለት አንደሚከብድ ተናግረው ምክንያቱ ደግሞ ተናጋሪው ማህበረሰብ በሌላ ቋንቋ መናገር ስለጀመረ መልሶ መናገሪያ ማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለዋል።


"አንድ ቋንቋ ሞቷል ማለት ልክ እንደ አማርኛ እና ኦሮምኛ የሚናገረው ማህበረሰብ የለውም ማለት ነው" የሚሉት በድሉ ዋቅጅራ ነገር ግን ሁለተኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሉትም ማለት አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።


ላቲን፣ ግሪክን እና ግዕዝን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ የሚናገሯቸው እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡


ለምሳሌ ግዕዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ላይ እንደሚውል ያስረዱት በድሉ(ዶ/ር) ለመናገሪያ ባይውልም ለስነ ከዋክብት ጥናት፣ ለስን ጽሁፍ፣ ታሪክን ለመረዳት ይረዳል ሲሉ አብራርተዋል።


አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በበኩላቸው የስነ ልሳን ባለሞያዎች ቋንቋን ሞቷል ወይም አልሞተም በለው ለመበየን የሚጠቀሙት ስነ ልሳን የተማሩበትን የውጪውን አለም ሳይንስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


እኛ የራሳችንን መመዘኛ መቀረጽ እንችላለን ብዬ አስባለው ሲሉ አስረድተዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ሞትን በተለያየ ደረጃ የሚበይን አንድ ብሔረሰብ እንዳለ ሰምቻለው አልያም አንብቤያለሁ። አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ከስጋው ስትለይ ነው እኛ ሞተ የምንለው፤ ነገር ግን እነሱ ሞተ አይሉም ምክንያቱም ልጆቹ፣ ሚስቱ እና ቤተሰቡ ሁሉ ስላሉ ብለው አስረድተዋል።


ስለዚህ ሞተ ሳይሆን ሌላ ቃል አላቸው መቃብሩም የሚሰራው ያን ታሳቢ ያደረገ ነው። ሀገር ሙሉ እያወቀው እንዴት ሞቷል ይባላል። ከዚያ እሱ የሚያውቃቸው የእድሜ እኩዮቹ በመላ ሲያልፉ ወደ ሞት ትንሽ ጠጋ ይላል፣ ሌሎች ያልፋሉ አሁንም ወደ ሞት ጠጋ ይላል ከዚያ ልጆቹ አልፈው ከሰው ትዝታ ጨርሶ ሲፋቅ ነው ሞተ የሚባለው ሲሉ አስረድተዋል።

ree

አሁን ግዕዝ እንዳለመታደል ሆኖ በምሁራን አካባቢ ነው የማይታውቀው እንጂ ብዙ ሰው ያውቀዋል። ስለዚህ የሞቱን ጉዳይ በዚያ ብንዳኛው፤ እኛ የራሳችንን መመዘኛ ብንይዝ ብለዋል አቶ ይኩኖአምላክ። ግዕዝ ከቋንቋዎቻችን አንዱ ነው ያሉት አቶ ይኩኖአምላክ ለዕለት ተዕለት አንነጋገርበትም፣ ለወደፊትም እንነጋገርበት በሚለውም እኔ አልስማማም ምክንያቱም አማርኛም ራሱ እራሱን ችሎ እየተነገረ ስላልሆነ ብለዋል።


ግዕዝ የንግግር ቋንቋ የማይሆነው ባለቤት ስለሌለው ሳይሆን ከንግግር ከወጣ ረዥም ጊዜ ስለሆ ነው አሁን እሱን ለመተካት የምንጨምራችው ቃላት ሌላ ቋንቋ ነው የሚያደርጉት አስፈላጊም አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።


በውይይቱ ላይ የተገኙት አቶ ጀማል አህመድ የተባሉ ተሳታፊ አንድን ቋንቋ በራሱ ከሃይማኖት መነጠል ይቻላል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል።


አቶ ደመላሽ የተባሉ ሌላ ተሳታፊ ደግሞ አንድን ቋንቋ ሞቷል ብለው ከበየኑ ወዲያ በዚያ ጉዳይ ላይ መነጋገር አወዛጋቢ እንደሆነ ተናግረው በሞተ ነገር ላይ የምንነጋገርበት ጉዳይ የለም ሲሉ ተችተዋል።


ቋንቋው ሞቷል ብለን ከበየንን ትክክለኛው መድሃኒት ማስቀመጥ የለብንም ወይ? ሲሉ የጠየቁት አቶ ደመላሽ ሞቷል ካልን በኋላስ ከ9ኛ ከፍል ጀምሮ ይሰጥ ማለት ምን ማለት ነው? መሰጠት ካለበትስ ከታች ክፍል አይሻልም ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል።


በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳን ባለሞያ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ስዩም፤ በቃል ብቻ የሚነገረን ቋንቋ አፍ የፈታበት ሰው ከሞተ፣ የሚናገረው ሰው ከጠፋ እና ተከታይ ካጣ ሞተ ልንል እችላለን ምክንያቱም እንደ ቅርስ ተቆፍሮ የሚወጣ ነገር ስለሌለ ብለዋል።


ነገር ግን እንደ ግዕዝ ያሉ ቋንቋዎች በአፍ መፍቻ መነገር ሳይሆን በጽሑፍ የዳበሩ፣ በአግልግሎታቸው፣ በማስተማሪያነታቸው፣ በዜማ እና በፍልስፍናችው ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ቋንቋዎችን የአፍ መፍቻ ተናጋሪ ስሌላቸው ብቻ ሞተዋል ማለት አንችልም ሲሉ የስነ ልሳን በለሙያ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ሀሳብ ተሰጥተዋል። ምክንያቱም ቋንቋው ህያው ሆኖ እያገለገለ ስለሆነ ሲሉ ተናግረዋል።

ree

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት መሆናቸውን የተናገሩ አንድ ተሳታፊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አለምን ከሚመሩ ታላላቅ ሀገራት መካከል የነበረችው፣ የጥንታዊ ስልጣኔንም መሰረት የጣለችው የግዕዝ ቋንቋ የህዝብ ቋንቋ በነበረበት ወቅት እንደሆነ አስታውሰዋል። “ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን” እያልን በተደጋጋሚ እንዘምራለን ስለዚህ ትልቅነትን የት ነው የምናገኘው? ከተባለ ስለ ታላቅነታችን ጥበብ እና ፍልስፍና ያያዙ መዛግብት እና ሰነዶችን መረዳት ስንችል ነው ሲሉ አስረድተዋል።


የኢትዮጵያ እውቀት የተቆረጠ እውቀት ነው የሚል እምነት አለኝ ያሉት ተሳታፊው ከግዕዝ ስንለይ እውቀታችንም ተቋርጧል ብለዋል። እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ በትምህርት ውስጥ ቋንቋው ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት ተሳታፊው የተቋረጠው ከወረራው በኋላ ነው ብለዋል።


እኛ ተምረናል ዶክትሬት ይዘናል ፕሮፌሰሮችም ብዙ አሉ ያሉት ተሳታፊው ግዕዝን ባለማውቃችን ግን ከሀገር በቀል እውቀት ጋር ተለይተን ነው ያለነው ሲሉ አስረድተዋል።

እኛም ይህ ክፍተት ተፈጥሮብናል፤ የድህነታችም አንዱ ምንጭ ይህ ነው የሚል እምነት አለኝ፣ ይህ የተቋረጠ ታሪክ ለማስቀጠል ግዕዝን ከታች ጀምሮ ማስተማር አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።


በድሉ ዋቅጅራ ለጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ በግዕዝ ቋንቋ አስፈላጊነት ላይ ማንም ጥርጥር እንደሌለው ተናግረው የኢትዮጵያ መሰረት ነው ብለዋል፡፡


የሀገሪቱ የትምህርት ስርዓት ከመጀመሪያው ሲነሳ ሀገር በቀል የሆነውን እውቀት እና አስተሳሰብ ትቶ ነው ያሉት በድሉ(ዶ/ር) ኢትዮጵያን የሚያህል ጥንታዊ ታሪክ ያላት ሀገር ክላሲካል ስተዲስ እንደሌላት አስረድተዋል፡፡


የግዕዝን ማስተማር አስፈላጊነት ላይ ምንም ጥርጥር የለም በዚህ እንስማማ ያሉት በድሉ(ዶ/ር) የሚያጨቃጭቀን የት ይጀመር የሚለው ነው ብለዋል፡፡


በድሉ(ዶ/ር) የግዕዝ ቋንቋ ሞቷል ብለሃል ታድያ ከሞተ ለምን በዚህ ላይ ለመወያየት አስፈለገ በሚል የተጠየቁትን ጥያቄ ሲመልሱም የቋንቋ የአሟሟት ሌላ ነው፣ ከሰው አሟሟት ጋር አይገናኝም፡፡ ቋንቋን ሞተ የምንለው ድብን ብሎ ጠፍቶ ማንም ተናጋሪ ፊደል እንኳን ሳይቀርጽለት የሚጠፋ ቋንቋ ነው የሚሉት ባለሞያው ነገር ግን እንደ ግዕዝ ከተናጋሪ ቢለይም በጣም በርካታ አገልግሎት ያለው ቋንቋ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡


"ይኩኖአምላክ እና የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳላችሁት እናንተ በተማራችሁበት ቋንቋ ሞቷል የሚለው ቃል የሚዘገንን ነው፤ እሱ ጨርሶ ለወደቁት ነው ካላችሁ መስማማት እንችላለን፤ ነገር ግን እውነታው ቋንቋው ተናጋሪ የለውም፡፡ ልክ እንደ አማርኛ እና ሌሎች ቋንቋዎች ጠዋት ተነስቶ የሚናገረው የለውም፣ ከዚያ ውጪ ግን ያለው ሃብት የትዬለሌ ነው ለዚህ ነው የምንጨቃጨቀው፣ እንማረው የምንለው ስንማርስ ከየት ጀምሮ ይሁን የምንለው’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡


ከየት ጀምሮ ይስጥ በሚለው ላይ ወይይት እና ጥናት ተካሂዶ ቋንቋውን መስጠጥ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡


አቶ ይኩኖአምለካ ግዕዝን ከሃይማኖት ለይተን ማየት እንችላለን ወይ በሚል ከአቶ ጀማል የቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "ከሃይማኖት ጋር መጀመሪያውኑ ቋንቋ አይገናኝም’’ ብለዋል፡፡


ግዕዝ ብዙ ጊዜ የክርስትና ቋንቋ ነው እንዲሁም አረብኛ ደግሞ የእስልምና ቋንቋ ነው ይባለል ይሄ ፍጹም ስህተት ነው ሲሉ አቶ ይኩኖአምላክ ተናግረዋል፡፡


ለምሳሌም ገድለ ላሊበላን ማየት ይቻላል ያሉት ባለሞያው ስለዚህ የእስልምና ቲዮሎጂ በግዕዝ ይገለጻል የክርስትናም ቲዮሎጂ በአረብኛ፣ በግዕዝ ፣በእንግሊዝኛ ይገለጻል ክርስቲያኑ በአረቡ አለም የሚገለገለው በአረብኛ ነው ብለዋል አቶ ይኩኖአምላክ፡፡


አቶ ይኩኖአምላክ ከስንተኛ ክፍል ጀምሮ ይሰጥ በሚለው ላይ ሃሳባቸው ሲሰጡ ንባቡን እና አካሄዱን ጥንቅቅ አድርጎ መማር አንዲቻል ከ4ኛ እስከ 8ኛ ከፍል እንዲማሩ አድርጎ ከ9ኛ ከፍል ጀምሮ ደግሞ በፍላጎት ማድረግ ቢቻል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ree

በስነ ልሳን መመህሩ እና ተመራማሪው በዘላለም ልየው(ፕ/ሮ) "እንደ ግዕዝ ያሉ ቋንቋዎችን ከተፈለግ ነፍስ ልንዘራባቸው እንችላለን ፡፡ ከፈለግን ድግሞ ጥናታዊ የእውቀት ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል ግን የተዘጋ ነገር አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡


የቤተሰብ አቅድ (family planning) አለ፣ የኢኮኖሚ እቅድ (economy planning) እንደሚያስፈልግም እናውቃለን፤ ልክ እንደዚሁ ሁሉ የቋንቋ (language planning) ያስፈልጋል ያሉት ዘላለም ልየው(ፕ/ር) በኢትዮጵያ ግን የቋንቋ እቅድ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡


በቋንቋ እቅድ፣ እየደከሙ ያሉ ቋንቋዎችን ማጠናከር፣ መደበኛ ቋንቋም ሆነው ብዙ ቃላት፣ ሰዋሰዋዊ ስርዓት፣ መዝገበ ቃላት ወይም የማስተማሪያ መጻሐፍት የሚስፈልጋቸውን ማገዝ ደግሞ የቋንቋ እቅድ አካል ነው ብለዋል፡፡


ግዕዝንም ካሰፈለገ በቋንቋ እቅድ ውስጥ አካትቶ ውስጡ የታጨቀውን የአስትሮኖሚ፣ የስነ ጽሁፍ፣ የእርሻ እና የመሳሰሉ እውቀቶችን እያወጣን መጠቀም እንችላለን ሲሉም አክለዋል፡፡

ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Recent Posts

See All
ጥቅምት 20 2018 - በሥራቅ አርሲ ዞን ባለንበት በጥቅምት ወር ብቻ 25 ሰዎች መገደላቸውን፣ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ተናገረ።

በኦሮሚያ ክልል በሥራቅ አርሲ ዞን ባለንበት በጥቅምት ወር ብቻ 25 ሰዎች መገደላቸውን፣ ይህንንም የተመለከተው በከባድና ጥልቅ የኃዘን ስሜት መሆኑን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ተናገረ። ቋሚ ሲኖዶስ በኦሮሚያ  ክልል በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር በጉና፣ በመርቲ፤ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋ

 
 
 

1 Comment


Mohammed Maru
Mohammed Maru
Oct 16

ግዕዝ አገልግሎቱ በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ብቻ መሆኑን በግልፅ ከተቀበልክ በኋላ፣ በተቃራኒው አረብኛ ደግሞ አገልግቱ በመስጊድ ውስጥ ያልቸወሰነ፣ብዙ ቤተእምነቶች የሚጠቀሙበት እና አለምአቀፋዊ ቋንቋነት ደረጃ የደረሰ መሆኑን እየታወቀ፥ ሁለቱን ቋንቋዎች ከዚህ ሁኔታ ለንፅፅር ማቅረብ፣ ድንቁርና እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። ሌላው፣ የግድ ለህፃናት ሁሉ ካልተሰጠ ሞተን እንገኛለን የሚለው ድርቅናም፣ዓላማው ከቋንቋው ይልቅ በህፃናት አእምሮ ላይ ለመትከል የተፈለገ ድብቅ ጉዳይ እንዳለ አያጠራጥርም። ግዕዝ የሃይማኖት ቋንቋ መሆኑን (መደረጉን) ለማወቅ፣ ለፊደላቱ የተሰጡትን ትርጉሞች ማይት በቂ ነው። የ"ሀ" የ"ለ" የ"ሐ" የ"መ" እና የ"ሠ"ን ትርጉም በታተሙ መፅሐፍቶች ሁሉ ማየት በቂ ነው። ከቻላችሁ መጀመሪያ ቋንቋውን "secularize" አድርጉት፣ነፃ አውጡት እና እንያችሁ። በተረፈ በተረትተረት አታደናቁሩን።

Like
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page