ጥቅምት 21 2018 - በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ጦርነቶች ቆመው እውነተኛ እርቅ እና ሰላም እንዲወርድ የንግዱ ማህበረሰብ ጠየቀ፡፡
- sheger1021fm
- 4 hours ago
- 3 min read
ነጋዴዎቹ ይህን የጠየቁት ትናንት "የንግድ ሚና ለሰላም ግንባታ'' በሚል ሀሳብ አዲስ አበባ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ባሰናዳው የፓናል ወይይት ላይ ነው።
የውይይቱ ተሳታፊ አደም ካሚል (ረ/ፕ) ኢትዮጵያ የምትታወቅበት የረዥም ጊዜ ታሪኳ ፍትህ እና ሰላም እንደሆነ አስረድተዋል።
ያ ባይሆን ኖሮ ነብዩ ሞሀመድ ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ አይልኩም ነበር ይህም የምንኮራበት ታሪክ ነው ሲሉ አስታውሰዋል።

ትናንት የፍትህ እና የሰላም ሀገር ከሆነች ዛሬ ምን ተፈጥሮ ነው? ችግሩ ምንድነው? የሚለውን ምሁራን እና የሃይማኖት አባቶች ትኩረት አድርገው በጥናት ሊለዩት ይገባል ብለዋል።
ሌላ የውይይቱ ተሳታፊ መሳሪያ አንስተው እየታገሉ ያሉት የእኛው እህት ወንድሞቻችን ናቸው በስልጣን ላይ ያሉትም እንደዛው የእኛው ናቸው እያፋጁን ያሉት ሃያላን ሀገሮች መሳሪያ እየሸጡልን ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
“ችግራችንን ለምንድነው በክብ ጠረጴዛ የማንፈታው? ሲሉ የጠየቁት ተሳታፊው መሳሪያ አምራች ሀገሮች ለአፍሪካዊያን እና ኋላቀር ሀገሮች መሳሪያ እየሸጡ ነው ይህም ለራሳቸው ለመበልፀግ እንዲሁም የእነሱ አሽከሮች ሆነን እንድንኖር ነው’’ ሲሉ ተናግረዋል።
ስለዚህ ፖለቲከኞች ይህን እንዴት መረዳት ያቅታቸዋል? ወይስ ሳይታወቃቸው ቀርቶ ነው ወይ? ከሆኑ ግን ማወቅ ይኖርባቸዋል ሲሉ ጠይቀዋል።
ሁሉም አሸናፊም ተሸናፊም የሚሆንበት መድረክ ቢፈጠር ሲሉ የጠየቁት ተሳታፊው ያኔ ሰላም ይመጣ ነበር ብለዋል።

ንግድ የሚሰራው ሰላም ሲሆን እንደሆነ እና ያለሰላም ደግሞ ምንም መስራት አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ያለውም አብዛኛው ሰው ገበሬ በሆነበት ሀገር ሽንኩርት ኪሎው 100 ብር የገባው በሰላም እጦት ምክንያት መሻገሪያ እያጣ ነው ብለዋል።
ሰላም ሊመጣ የሚችለው ደግሞ መንግስትም፣ ተቃዋሚዎችም በእውነት ስለ እውነት ከልብ እርቅ እና ሰላም ሊፈጥሩበት የሚችሉት መድረክ ሲፈጠር ነው ሲሉ አስረድተዋል።
አቶ ሻምበል ሚደቅሳ የተባሉ ነጋዴ እና የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው በሰላም እጦቱ ምክንያት ንብረቱ የሚዘረፈው፣ መኪናው የሚቃጠለው፣ ሀብቱ የሚወድመው የነጋዴው መሆኑን ጠቁመዋል።
የእኛ ጥያቄ ጦርነት፣ ተኩስ እና ጥይት መቀባበል ይቁም ነው የሚሉት አቶ ሻምበል ሚደግሳ በአገራችን ሰላም ተንፍሰን እንኑር ሲሉ አክለዋል።
መደማመጥ ይኑር መናናቅ ይቁም ያሉት ተሳታፊው ካልተስማማን፣ ካልተደማመጥን በስተቀር የሰላም ጥናት፣ የሰላም ንግግር፣ ንግድ እና ሃይማኖት ፣ ሃይማኖት እና ሰላም ብንል እንዴት ይሆናል ሲሉ ጠይቀዋል።
ስለዚህ የመንግስት አካልም ጥይት የሚተኩሱትን ሳይንቅ ተኩስ አቁም አውጆ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁኔታዎችን አመቻችቶ ተኩስ አቁሞ ወደ እርቅ መሄዱ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰላም ከሌለ በኪሴም፣ በባንክም ፣ በድርጅቴም ላይ ያለው ገንዘብ የእኔ አይደለም የሚሉት አቶ ሻምበል የሚነጥቀው ሌላ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የንግዱ ዘርፍ የሚታወክበት ጉዳይ መኖሩም በውይይቱ ተነስቶ ነበር፡፡
ሌላው የወይይቱ ተሳታፊ ሥነ ምግባር ያለበት ንግድ የት ነው ያለው? ሲሉ ከጠየቁ በኋላ ስራው በሙስና እና ቀልጣፋ ባልሆነ አገልግሎት ታውኳል ሲሉ ተናግረዋል።
ነጋዴዎችም በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የተዘጋውን ለመክፈት ህግን ያልተከተለ መንገድ ይጠቀማል ይህ መታረም ካልቻለ እንደ የሰላም እጦት ችግር ሊሆን ይችላል ብለዋል።

በወይይቱ ላይ የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት መጋቢ ታምራት አበጋዝ ነፍጥ ማንሳትም ሆነ ጫካ መግባት ለአገር መፍትሔ እንደማያመጣ አስታውሰው የችግራችን መፍቻ ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ለንግግር ክፍት መሆን አለባቸው ያሉት መጋቢ ታምራት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ትርጉም ሳይሰጥ፣ ሰዎች ሳይሸማቀቁ ሃሳባቸውን በነፃነት ማቅረብ የምችልበት ምክንያቱም የምናቀርባቸው ሀሳቦች ለመፍትሔ እንጂ ለጸብ ስላልሆነ ብለዋል።
ሰላም እንዲጸና ፍትህ አስፈላጊ መሆኑንን የሚያስረዱት መጋቢ ታምራት እውነት ፍትህ እና ርትዕ በሌለበት እንዲሁም ሙስና ባየለበት ስለ ሰላም ማውራት ከባድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው በእጃችን ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመንከባከብ መጠበቅ ካልቻልን እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የሚታዩትን ግጭቶች መፍታት ካልቻልን አንድ ቀን ሌሎች ሰፈር እያየነው ያለው ግጭት እና ጥፋት አገር እንዳያሳጠን አርቆ ማሰብ እና በጋራ መስራት ጊዜው የሚጠብቀው ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዕያ(ፕ/ር) የውስጥ ብሶቶች አሉ እነሱ ላይ መነጋጋር አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው በትክክል መግባባት ላይ መድረስ ያለብን በጣም በርካታ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች አሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልጉት መሪዎች ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ መሪ ማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ማለት አይደለም፤ መሪ ማለት የቀበሌ ፣የወረዳ መሪ ጭምር ማለት ነው፤ የነገዋ ኢትዮጵያ የነገይቷም፣ የዛሬይቷም ኢትዮጵያ የእኔ ነች የሚል መሪ ያስፈልጋታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ለገንዘብ ሳይሆን ለህሊናው የሚገዛ መሪ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ያሉት መስፍን አርዕያ (ፕ/ር) ይህን ደግሞ መፍጠር የምንችለው ተነጋግረን መግባባት ስንችል እና ሰላም ስናዎርድ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ ሞሃመድ በሰጡት ሀሳብ የሰላም መደፍረስ ካለ ስራ መስራት ስለማይቻል በአገር ሰላም እንዲወርድ ጠይቀዋል፡፡

ሰላም በሌለበት ኢንቨትመንትም ሆነ የስራ እድል መፍጠር አይቻልም ያሉት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ ሞሃመድ ለዚህም የንግዱ ማህበረሰብ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም በፓርላማ ቀርበው ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአገሪቱ የቆየው የእርስ በእርስ ጦርነትን መቆም አለበት ነገር ግን ኢትዮጵያ ደካማ ሆና እንድትኖር ፤ በሁለት እግሯ እንዳትቆም የሚሹ የሚሰሩ ሀገራት ባሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያዊያን የሀገር ጥቅምን ለይተው ማወቅ ካቃታቸው ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ለጠላት ፍላጎት ተላልፈው ከተሰጡ የተሟላ ሰላም ማምጣት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s












Comments